ቀጥታ፡

በመዲናዋ ያሉ የቱሪዝም መስህቦች ለከተማዋ ገጽታ ግንባታ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦በመዲናዋ ያሉ የቱሪዝም መስህቦች ለከተማዋ ገጽታ ግንባታ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን  ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን አንደኛውን የቱሪዝም ፎረም ከታህሳስ 5 እስከ ታህሳስ 7 ቀን 2018 ዓ.ም በመዲናዋ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ፤ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ትኩረት በአዲስ አበባ በርካታ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች መገንባታቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም የነባር መዳረሻዎችን  መሰረተ ልማት በማሻሻል ለቱሪዝም ፍሰት ምቹ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ዘርፉን በይበልጥ ለማስተዋወቅና ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማሳደግ ከታህሳስ 5 እስከ ታህሳስ 7 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ ፎረም ለማካሄድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የፎረሙ ዋና ዓላማ ህብረተሰቡ በከተማዋ ስለሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖረውና የጉብኝት ባህሉን እንዲያጎለብት ማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈ ባለድርሻ አካላትን በአንድ መድረክ በማገናኘት ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሆነም አብራርተዋል።

ከኹነቶቹ መካከል የቱሪዝም ንግድ አውደ ርዕይና ኤግዚቢሽን፣ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶችን የሚዳስስ የፎቶ አውደርዕይ፣ ቱሪዝምን በቴክኖሎጂ ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ የዲጂታል ውጤቶችን ይፋ ማድረግ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። 

በመድረኩ በቱሪዝም እድገት ላይ የሚያጠነጥን የፓናል ውይይት እንደሚደረግም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም