ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት ጠንካራ ተቋምና አስተማማኝ የፋይናንስ ሥርዓት ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ በፍጥነት እያደገ ላለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቀጣይነት ጠንካራ ተቋማት፣ አስተማማኝ የፋይናንስ ሥርዓት እና ብቁ የሰው ሃይል መኖር ወሳኝ መሆናቸውን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ለተመሰከረላቸው የኢትዮጵያ ሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ስያሜ ይፋ የማድረግ እና የስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ እንዳሉት የኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫ ጠንካራ ተቋማትን አስተማማኝ የፋይናንስ ስርዓት እና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያስቀጥል የሰለጠነ የሰው ኃይል ይጠይቃል።

የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ወደ ስራ መግባት የፋይናንስ ዘርፉን ትራንስፎርሜሽን ለማሳለጥ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለፋይናንስ ስርዓቱ የጀርባ አጥንት ከመሆን ባለፈ አስተማማኝ የፋይናንስ ዘርፍ እንዲፈጠር፣ ህብረተሰቡ ስለፋይናንስ ዘርፉ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው እና ለውሳኔ ሰጪዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ነው ያሉት።

ይህም የኢኮኖሚ ዕድገትና ሽግግርን በማሳለጥ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።


 

ካሁን ቀደም የሂሳብ ባለሙያዎች ማረጋገጫ የሚቀበሉት ከውጭ ተቋማት መሆኑን አስታውሰው፥ ኢንስቲትዩቱ ይህንን ተግባር በሀገር ውስጥ ማከናወን የሚያስችል ነው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ በተቋማት አሠራር ግልፅነት እና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ የሂሳብ አያያዝ፣ ኦዲት እና የፋይናንሺያል ሪፖርት መረጃዎችን የማስተዋወቅ እና የማሳደግ አላማ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ዘመናዊ፣ ግልጽ የሆነና ለችግር የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የራሱ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።


 

ኢንስቲትዩቱ ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ የዘርፉ ተቋማት ፈቃድ ባላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች የታገዘና ደረጃውን የጠበቀ የሂሳብ ሪፖርት እንዲያዘጋጁ ያስችላቸዋል።

ይህም የሂሳብ ሪፖርቶች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟሉ በማድረግ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ አጎናፍር በኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ቢኖሩም የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ወደ ሥራ መግባቱ በዘርፉ ብቃት ያለው ከፍተኛ የሰው ሃይል ማፍራት እንደሚያስችልም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም