በባሕር ዳር እየተከናወኑ የሚገኙ ሁለንተናዊ የልማት ተግባራት የከተማዋን ዕድገት የሚያፋጥኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በባሕር ዳር እየተከናወኑ የሚገኙ ሁለንተናዊ የልማት ተግባራት የከተማዋን ዕድገት የሚያፋጥኑ ናቸው
ባሕርዳር፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፡- በባሕር ዳር በሕብረተሰቡ ተሳትፎና ድጋፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ሁለንተናዊ የልማት ተግባራት የከተማዋን ዕድገት የሚያፋጥኑ መሆናቸውን ሰልጣኝ አመራሮች ገለጹ።
በባሕርዳር ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ መካከለኛ አመራሮች በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራትን ተመልክተዋል።
ከአመራሮቹ መካከል አቶ አብርሃም አበጀ ፤ በመደመር መንግስት እሳቤ እየተከናወኑ ያሉ የባሕር ዳር ከተማ ልማቶች ዕድገቷን የሚያፋጥኑ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
በተለይ የኢንዱስትሪ፣ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምና የኮሪደር ልማት ተግባራት ለስራ እድል ፈጠራና የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻነት የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።
ከጉብኝቱና ከስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ሰላምን ለማፅናትና ልማትን ለማስቀጠል ማሕበረሰቡን በማስተባበር ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በባህር ዳር የጎበኙት የኢንዱስትሪ መንደር ለከተማው፣ ለክልሉና ለሀገር ዕድገት መፋጠን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የተናገሩት ሌላኛዋ ሰልጣኝ ወይዘሮ ነኢማ መሀመድ ናቸው።
ተኪና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶች በስፋት በመመረት ላይ እንደሚገኙ መመልከታቸውን አንስተው፤ ይህም በጠንካራ መሪዎች የሀገር ብልጽግና መረጋገጥ እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
በሕብረተሰቡ ተሳትፎና ድጋፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራት የከተማዋን ዕድገት የሚያፋጥኑ መሆናቸውንም አክለዋል።
ስልጠናውም ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል ዕድገትን ለማፋጠን የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል።
ሀገርን ከድህነት ለማላቀቅ በመደመር መንግስት እይታ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን በመስክ ምልከታው አረጋግጫለሁ ያሉት ደግሞ አቶ ኃይለማርያም ሽፈራው ናቸው።
የልማት ፀጋዎችን በመለየት ወደ ስራ በመለወጥ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል ዕውቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ብርሃን ንጉሴ፤ በጉብኝቱ በከተማዋ የኢንዱስትሪ መንደርን፣ የኮሪደር ልማትን፣ መሶብ የአንድ የአገልግሎት መስጫ ማዕከልና የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዮም ተደራሽ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የባሕርዳር ከተማን የልማት ስራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠልና የልማት ተግባራትን በማስተሳሰር ብልፅግናን ለማረጋገጥ ይበልጥ የሚያነሳሳ እንደሆነ ተናግረዋል።