በኢትዮጵያ የዳበረ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ እንዲጎለብት እየተሠራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የዳበረ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ እንዲጎለብት እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የዳበረ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
ምክር ቤቱ ያዘጋጀው'' የፖለቲካ ተሳትፎ መመሪያ መፅሐፍ ''ተመርቋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ በሀገሪቱ ጠንካራ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቁና ዝግጁ ሆነው በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችል የፖለቲካ ተሳትፎ መመሪያ መፅሐፍ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
ጠንካራ እና አማራጭ እሳቤን ማቅረብ፣ የተሳካ የህዝብ ግንኙነትን በሚገባ መተግበር፣ የአካታችነትና አሳታፊነትን ባህል መገንባትን ጨምሮ ለስኬታማ የፖለቲካ ምህዳር ወሳኝ የሆኑ ሰፋፊ ተግባራትን እንደሚያጠቃልልም ነው የገለፁት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ንዋይ በበኩላቸው፤ የመመሪያ መፅሐፉ ፓርቲዎች በምርጫ ሂደት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲሁም የውስጠ ፓርቲ አስተዳደርን መያዙን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች በመደበኛ ጊዜያቸው ከሚያከናውኗቸው ተግባራት በተጨማሪ ለሀገራዊ ምርጫ ተሳትፏቸው አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል።
መጽሐፉ በፖለቲካ ፖርቲዎች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች ቶሎ እንዲፈቱ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ቀድሞ በመለየት መፍትሔ ለማስቀመጥና የፖለቲካ አለመግባባቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ ለማድረግ እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች መመሪያ መፅሐፉን በመጠቀም እና በማዳበር ለሀገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጋራ ምክር ቤቱና እርስ በእርስ ስለሚኖራቸው ግንኙነት በተመለከተ የፖለቲካ ተሳትፎ መመሪያ መፅሐፉ ሐሳቦችን መያዙን ተናግረዋል።