ቀጥታ፡

በመደመር መንግስት እሳቤ የሀገርን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት እንሰራለን - አመራሮች

ሰቆጣ፣ ገንዳ ውሃ፣ ደብረ ብርሃን፣ ወልዲያ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦በመደመር መንግስት እሳቤ የአካባቢን ፀጋ  በማልማት የሀገርን ብልፅግና ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ የአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢ አመራሮች ገለፁ።

‘’በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ’’ በሚል መሪ ሀሳብ ስልጠና የወሰዱ አመራሮች የማጠቃለያ ፕሮግራምና የልማት ስራዎች ጉብኝት ተካሄዷል።

በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሰቆጣ ከተማ ስልጠና ተሳታፊዎች መካከል አቶ አሻግሬ ደሳለኝ እና አቶ ታረቀ አለሙ እንዳሉት፤ የመደመር መንግስት እሳቤ በህብረ ብሄራዊ መርህ ለሀገር ግንባታ መትጋት ነው።


 

የግብርናውን ምርታማነት በማሳደግ ከተረጂነት የመላቀቅ ርዕይን ለማሳካት ህብረተሰቡን በማሳተፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አክለዋል።

ሌላዋ የስልጠናው ተሳታፊ ወይዘሮ ፀገነት ደምሴ በበኩላቸው፤ ከስልጠናው ባገኙት እውቀት ህብረተሰቡ የተፋጠነ አገልግሎት እንዲያገኝ ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።


 

በተመሳሳይ በዞኑ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማጠናከር የሀገሪቱን የብልፅግና ጉዞ የሚያፋጥኑ ናቸው ያሉት ደግሞ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃና አካባቢው ያሉ የልማት ስራዎችን የጎበኙ ሰልጣኞች ናቸው። 

የጉብኝቱ ተሳታፊ አቤሴሎም ጌታቸው እንዳሉት፤ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነውን አካባቢ ለአልሚዎች ይበልጥ ክፍት  እንዲሆን የአመራርነት ሚናቸውን እንደሚወጡም አክለዋል። 


 

ዮናስ ሞላልኝ እና አቶ አስማማው አለባቸው በበኩላቸው፤ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርግ ሀብትን  የማመቻቸት ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

መንግስት ያስቀመጣቸውን እድገት ተኮር ኢንሼቲቮች አሟጦ ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ እያሱ ይላቅ እንዳሉት፤ አመራሩ በጉብኝቱ የተመለከቷቸውን የልማት ተግባራት እንደየአካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታ ማስፋትና የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። 

የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማጠናከር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንን የገለፁት ደግሞ  የሰሜን ሸዋ ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ደምሰው መንበሩ ናቸው።

ባለፉት አምስት ወራት 32 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 211 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል።


 

የጉብኝቱ ተሳታፊ አቶ ጥላየ ገብርየ እንዳሉት፤ ስልጠናውና በጉብኝቱ ሀገሪቱን ያለችበትን የእድገት ደረጃ ለመገንዘብ ያስቻለ ነው።

ስልጠናው ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ኤልሳቤት ሀይለመስቀል  ናቸው።


 

የወልዲያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው፤ ከስልጠናው የተገኘውን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ አገርን የመገንባትና የማዘመን ስራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል። 

ከተማችንን የቱሪስት መዳረሻ  ለማድረግ  ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሃብቶችን ማልማት ላይ ጠንክሮ ለመስራት  የቤት ስራ የሰጠ ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም