ቀጥታ፡

አመራሩ በተደመረ አቅምና እውቀት ህዝብን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት ሊያገለግል ይገባል

ደሴ/ባሕርዳር፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፡-በተደመረ አቅምና እውቀት አመራሩ ህዝብን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት ሊያገለግል ይገባል ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ ተናገሩ።

"የመደመር መንግስት እይታ፣የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሀሳብ በደሴና ባሕርዳር ለመካከለኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል።


 

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ፤ በየደረጃው ያለው አመራር ለልማት ከመትጋት ባለፈ በቀናኢነት ህዝብን ለማገልገል የላቀ ዝግጁነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል።

በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ጭምር የተሟላ ስብእና በመላበስ ለችግሮች መፍትሄ መሻት፣ለሰላምና ልማት በጋራ መትጋት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም አመራሩ በስልጠናው ያገኘውን ግንዛቤ በመሰነቅ በተደመረ አቅምና እውቀት ህዝብን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት ለማገልገል መዘጋጀት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የክልሉ መንግስት ከምንም በላይ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አንስተው የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን፣ በየአካባቢው ያሉ እምቅ ሃብትና ጸጋዎችን በማልማት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ የተቀናጀ ጥረታችን ይቀጥላል ብለዋል።


 

ከስልጠናው ታሳትፊዎች መካከል ወይዘሮ ሶፊና አደም እና አቶ ኡመር አሰፋ፤ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ተግባር ላይ በማዋል ውጤት ለማምጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በባሕርዳር ከተማ የማጠቃለያ መድረክ ላይ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ሁሴን፤ ‎በግብርና፣በኢንዱስትሪ፣ በከተሞች መሰረተ ልማትና በቱሪዝም ብዝሃ ኢኮኖሚ ልማት ዘርፎች ላይ የተሰጡ ስልጠናዎችን በተቀናጀ መልኩ በተግባር መግለጥ ይገባል ብለዋል።


 

የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ጥላሁን፤ ‎የልማት እቅዶችን ማሳካት የሚቻለው በትብብር በመስራት በመሆኑ በዚሁ ልክ አመራሩ ዝግጁ ሆኖ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

የስልጠናው ተሳታፊ አመራሮችም በተደመረ አቅምና እውቀት ህዝብን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም