በአማራ እና አፋር ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች የልማት ትስስሮችን ለማጠናከር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ እና አፋር ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች የልማት ትስስሮችን ለማጠናከር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው
ደሴ፤ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦በአማራ እና አፋር ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች የሰላም ግንባታና የልማት ትስስሮችን በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የሁለቱ ክልሎች የሰላምና ፀጥታ አመራሮችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በአዋሳኝ አካባቢዎች በዘላቂ ሰላምና የልማት ስራዎች ዙሪያ በኮምቦልቻ ከተማ ውይይት አድርገዋል።
የአማራ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር)፥የክልሎቹ አጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች ጠንካራ አብሮነት ያላቸው መሆኑንና የሚጋሯቸው በርካታ እሴቶች እንዳሏቸው አንስተዋል።
እነዚህን እሴቶች በማጎልበት የሰላም ግንባታና የልማት ትስስሮችን ይበልጥ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አጽኖት ሰጥተዋል።
በመሆኑም በሁሉቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሰላም ግንባታን የማጎልበትና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
በተለይም የመሰረተ ልማትና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማጠናከር እንዲሁም ሰላምን በማጽናት ረገድ በቀጣይ የተቀናጀ ጥረት እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል።
የአፋር ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አህመድ ሁመድ በበኩላቸው፥ በሁሉቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሰላምና የልማት ስራዎች ጉዳይ ይበልጥ ተቀራርበን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በመሰረተ ልማትና የገበያ ትስስር እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በመሆኑም እነዚህን አጠናክሮ በመቀጠል የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይበልጥ ተቀናጅተን እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
ግጭት ሰባቂዎችን በጋራ መመከትና የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ይገባል ያሉት ደግሞ
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቸሩጌታ ገነነ፤ በኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በተለያዩ አካባቢዎች ከልማት ይልቅ ግጭትና አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚጥሩ የጥፋት ተልእኮ ያነገቡ አካላት ስለመኖራቸው አንስተው ሰላምን ማጽናትና ለልማት መትጋት የሁላችንም የጋራ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በመሆኑም በአፋርና አማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያጠናክሩ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አጽዕኖት ሰጥተዋል።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምስራቅ እዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል፤ በሁሉም አካባቢዎች ዘላቂ ሰላምን ማስጠበቅና የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት እውን ማድረግ የጋራ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በተለይም በአካባቢው በስፋት የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል፣ የመሳሪያና ሌሎችም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን በጥብቅ መከታተልና በጋራ መከላከል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በመድረኩ የፌዴራል፣ የሁለቱ ክልልች እንዲሁም የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የፀጥታ አባላት እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።