ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊያን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሠራች ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊያን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለፁ።

በአፍሪካ ሕብረት አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 17ኛው የአፍሪካ የመከላከያ መሪዎች ጉባዔ ተጠናቋል።

ጉባኤው አህጉሪቱ እያጋጠሙ የሚገኙትን ሽብርተኝነት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሌሎች የደኅንነት ችግሮችን በተባበረ ክንድ መፍታት ላይ ያለመ ነው።

መሪዎቹ የአፍሪካን የሠላምና የፀጥታ ችግሮች የሌላ አካል ጣልቃ ገብነት ሳይስፈልግ እንዴት በራስ አቅም ብቻ መፍታት እንደሚቻል በዝርዝር ተወያይተዋል።


 

ለቀናት በልዩ ልዩ አፍሪካዊ ጉዳዮች ሲመክር የቆዬው የመከላከያ መሪዎች ጉባኤ ቀጠናዊ ሠላምና መረጋጋትን ማስፈን፣ በሶማሊያ አልሸባብን ማስወገድ፣ በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ፣ ለሠላም ማስከበር ተልዕኮ የፋይናንስ ድጋፍ በሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቶ የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ኢትዮጵያ ለሠላም ባላት ጠንካራ አቋምና ተምሣሌትነት ተመርጣ ጉባኤውን ለተከታታይ ዓመታት እያስተናገደች መሆኗን ያነሱት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊያን ለመፍታት እየሠራች እንደምትገኝም ገልጸዋል።

ጉባኤው በአፍሪካ የሚስተዋል ችግሮችን በፍጥነት የሚፈታ የተባበረ የአፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል አስፈላጊነት ላይ መወያየቱን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለአህጉሪቱ ያላት አስተዋፅኦ የተንፀባረቀበት ጉባኤ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሶማሊያ ሕዝብ ሠላም ላበረከተው አስተዋፅኦ በስብሰባው ከፍተኛ እውቅና መሰጠቱን ያወሱት በመከላከያ የዓለም አቀፍና የጎረቤት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጄኔራል ሰብስቤ ዱባ በቀጣይም የአህጉሪቱን ችግሮች በትብብር እየፈቱ ለመሄድ ከስምምነት መደረሱን ገልፀዋል።


 

ሁሉም የአፍሪካ አባል ሀገራት የሚሳተፉበት የአፍሪካ የመከላከያ መሪዎች የሠላምና ደኅንነት ጉባኤ በየዓመቱ የሚካሄድ መሁኑም ተመላክትል።

17ኛውን የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ እና 20ኛው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞችና የደህንነት ኃላፊዎች ስብሰባ ከህዳር 29 እስከ ታህሳስ 2 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መካሄዱን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኢዜአ የላከው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም