ቀጥታ፡

የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የአጋር አካላት ሚና ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር የአጋር አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።

የጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ የህፃናትና ወጣቶች ጤና አጠባበቅ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ አካሒዷል።


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች።

በተለይም የእናቶችና ህፃናት ጤና አጠባበቅ እና ተደራሽነት ላይ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

እነዚህ ስኬቶች በመንግስት  ቁርጠኝነት እና በአጋር አካላት ያልተቋረጠ  ድጋፍ የተገኙ መሆናቸውን ገልፀዋል።


 

ኢትዮጵያ የእናቶችና ህፃናት ጤና በሁሉም የጤና ተቋማት በተሟላ መልኩ መስጠት የሚያስችል ጥረት እያደረገች ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማጠናከር የአጋር አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የእናቶችና የህጻናት ሞትን ለመቀነስ ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት ዕቅድ ነድፋ እየሰራች መሆኑን አንስተዋል።


 

ለዚህ ሥራ ይበልጥ መጠናከር የሚውል የሀብት ማሰባሰብ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው እስካሁንም ከአጋር አካላት ከ160 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሃብት መሰብሰቡን ነው ያነሱት።

ይህ ሃብት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለሦስት ዓመታት ጥቅም ላይ እንደሚውል በመጥቀስ የሀብት ማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የተሰበሰበው ሃብት ለህክምና ቁሳቁስና ግብዓት፣ ለጤና ተቋማት ግንባታ፣ ለጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታና መሰል ስራዎች እንደሚውል ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል።


 

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደርና የአጋር አካላት የሃብት ማሰባሰብ አስተባባሪ ክርስቲን ፒሬን፥ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ውጤት የሚበረታታ ነው ብለዋል።

በተለይም የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ሁሉም አጋር አካላት የሚከናወኑ ተግባራትን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው መሰል የሃብት ማሰባሰብና የድጋፍ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም