ኢንስቲትዩቱ የባዮቴክኖሎጂ ምርምሮችና ግኝቶችን ለማስተዋወቅ የተቀናጁ ተግባራትን እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ የባዮቴክኖሎጂ ምርምሮችና ግኝቶችን ለማስተዋወቅ የተቀናጁ ተግባራትን እያከናወነ ነው
ሮቤ ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባዮቴክኖሎጂ ምርምሮችና ግኝቶችን ለኅብረተሰቡ ለማስተዋወቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጁ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።
የኢንስቲትዩቱ የግብርና ባዮ-ቴክኖሎጂ የደቡብ ምሥራቅ መድረክ (ኦፋብ ኢትዮጵያ) ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የባለድርሻ አካላት ዐውደ ጥናት በባሌ ሮቤ አካሂዷል።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ባዮ -ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ታደሰ ዳባ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በባዮ ቴክኖሎጂ ሳይንስ የግብርናው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው።
ቴክኖሎጂው በግብርናው መስክ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለአብነትም በባዮ ቴክኖሎጂ ሳይንስ በቆሎና የጥጥ ዝርያ ላይ እየተካሄዱ የሚገኙ ምርምሮች ተስፋ ሰጪ ውጤት ማምጣታቸውን አንስተዋል።
የባዮቴክኖሎጂ ሳይንስ ጥቅምን በሕብረተሰቡ ዘንድ በአግባቡ እንዲታወቅና ተደራሽ እንዲሆን ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ ለመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር መሰራቱን አመልክተዋል።
የባዮ ቴክኖሎጂ ሳይንስ በተለይ የግብርናው ምርታማነት ላይ ማነቆ የሆኑ የሰብል በሽታዎች፣ አረምና ሌሎች ችግሮችን ለማቃለል የሚያግዝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ ተስፋዬ ዲሳሳ (ዶ/ር) ናቸው።
በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት በቆሎን በማዳቀል ዘርፍ የተካሄዱ የምርምር ሥራዎች በሽታን የሚቋቋምና ምርታማነትን የሚያሻሽል ዘር መገኘቱን አንስተዋል።
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ፣ ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት በዛብህ ወንድሙ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራ በተጓዳኝ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በተለይ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተሻሻሉና የምርጥ ዝርያዎችንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በምርምር ተደራሽ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
የተካሄደው መድረክም የተገኘውን ውጤት ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው አንስተዋል።
የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በተካሄደው የባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ መድረክ ላይ የምርምር ውጤቶችና የዘርፉን እምቅ አቅም ለኅብረተሰቡ ለማስተዋወቅ የሚረዱ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።