ዩኒቨርሲቲው የክልሉን የሰው ሃብት እውቀትና ክህሎት ለማጎልበት በትኩረት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የክልሉን የሰው ሃብት እውቀትና ክህሎት ለማጎልበት በትኩረት እየሰራ ነው
ባህር ዳር፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦የክልሉን የሰው ሃብት እውቀትና ክህሎት ከማዳበር ባለፈ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅምን የማሳደግ ተግባርን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል ስቴት ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
ስቴት ዩኒቨርሲቲው አዲስ የተቋቋመበትን አዋጅ እና ደንብ ለማስተዋወቅ ያለመ የውይይት መድረክ ዛሬ አካሄዷል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ማተብ ታፈረ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በክልሉ ያለውን የሰው ሃብት የእውቀትና የክህሎት ክፍተት በመሙላት እንዲሁም የመፈጸምና የማስፈጸም አቅምን የማሳደግ ትልቅ ኃላፊነት አለበት።
ስቴት ዩኒቨርሲቲው የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን ከመስጠት በተጨማሪ ችግር ፈቺ የምርምርና የማማከር ስራዎችን እንደሚያከናውን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማማከር ስራዎችን የውስጥ ገቢን በሚያሳድግ አግባብ እንደሚያከናውን ገልጸው በጥናት ላይ የተመሰረቱ አጫጭር ስልጠናና የረጅም ጊዜ ትምህርቶችን እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግስት በየጊዜው በሚያደርገው ግምገማ ትልቁ ክፍተት የሰው ሃብት ዕውቀትና ክህሎት እንዲሁም የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ማነስ እንደሆነም የሚታወቅ ነው ብለዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም ቀደም ሲል የአማራ ክልል የአመራር አካዳሚ ይባል የነበረውን ተቋም ወደ ስቴት ዩኒቨርሲቲነት በማሳደግ በተሻለ አቅም ስራዎችን እንዲያከናውን እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ስቴት ዩኒቨርሲቲው በእውቀትና በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል የማፍራት ሚናውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ በየደረጃው ያለው የዩኒቨርስቲው ሰራተኛም ይህንኑ ታላቅ ኃላፊነት በመረዳት ተግቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በመድረኩም የስቴት ዩኒቨርስቲው አመራሮችና ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።