በክልሉ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ነቀምቴ ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና ተሳትፎ የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
''አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማህበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማህበራዊ እድገት'' በሚል መሪ ሀሳብ የአካል ጉዳተኞች ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በነቀምቴ ከተማ ተከብሯል።
መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አብዱላሂ አህመድ፣ በክልሉ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት እና ተሳትፎ ለማሳደግ በተሰራው ስራ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
አካል ጉዳተኞችን ለማካተት፣ ለማሳተፍ እና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የወጡ ህጎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በክልሉ የአካል ጉዳተኞች የተሀድሶ ማዕከል ማቋቋም፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ መፍጠር እና ተያያዠ ስራዎች መሰራታቸውንም አስረድተዋል።
በቀጣይም በክልሉ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ደራራ ጣፋ እንደተናገሩት፤ ከለውጡ ወዲህ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰፊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው።
ማህበረሰቡ አካል ጉዳተኝነትን በተመለከተ ያለው ግንዛቤ እንዲሻሻል ለማድረግም የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ አካል ጉዳተኞችን በማህበር በማደራጀት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የነቀምቴ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ መላኩ ጌታሁን (ረዳት ፕሮፌሰር)፤ በከተማው ሁሉንም ማህበረሰብ ታሳቢ ያደረገ የልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ በሚያሳድጉ ተግባራት ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሰራበት ይሆናል ብለዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ኦላኒ አብዲሳ እንደተናገሩት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው ትኩረት እየተሻሻለ መጥቷል።
መልካም ጅምሮች ቢኖሩም አሁንም አንድ አንድ የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች ለአካል ጉዳተኞች የማይመቹ ሁኔታዎች በመኖራቸው መስተካከል አለበት ብለዋል።
በክልሉ የአካል ጉዳተኛ ተሀድሶ ማዕከላትን ለማቋቋም እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑንም አካል ጉዳተኞች ተናግረዋል።