አውደ ጥናቱ ለኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሊየር ኃይል ልማት ቀጣይ ስራዎች መደላድል የሚሆን ግንዛቤ ተፈጥሮበታል - ኢዜአ አማርኛ
አውደ ጥናቱ ለኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሊየር ኃይል ልማት ቀጣይ ስራዎች መደላድል የሚሆን ግንዛቤ ተፈጥሮበታል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦አውደ ጥናቱ ለኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሊየር ኃይል ልማት ቀጣይ ስራዎች መደላድል የሚሆን ግንዛቤ የተፈጠረበት መሆኑን የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ገለጸ።
የመጀመሪያው ብሔራዊ የኒውክሊየር ኃይል መርሃ ግብር ሚና እና ኃላፊነት የተቋም ትግበራ አውደ ጥናት ምክክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሽፈራው ተሊላ በዚሁ ወቅት፥ የኒውክሊየር ኃይል ለኢነርጂ፣ ለግብርና፣ ለጤና እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገለጸዋል።
የዚህ ኃይል አጠቃቀም በዓለም አቀፍ ሕግ የሚመራ መሆኑን ገልጸው ሀገራት ሊከተሏቸወ የሚገቡ ቅደም ተከተሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በአውደ ጥናቱ በሀገር ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላት እና የሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማት መሳተፋቸውንና ግንዛቤ መፈጠሩን ተናግረዋል።
የኒውክሊየር ፕሮግራሙ ሀገራዊ ፕሮጀከት በመሆኑ ህብረተሰቡ ለስኬቱ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ማስቻል ላይ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።
በአውደ ጥናቱ በዓለም አቀፍ የሕግ ማእቀፎች እና ሊከናወኑ በሚገባቸው ስራዎች ላይ ውይይት መደረጉንም አመላክተዋል።
የተቋማት አቅም እና የሰው ኃይል ግንባታ ሌላኛው በአውደ ጥናቱ በስፋት የተዳሰሰ መሆኑን ጠቁመዋል።
አውደጥናቱ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሊየር ልማት ቀጣይ ስራዎች መደላድል የሚሆን ግንዛቤ የተፈጠረበት መሆኑን ገልጸዋል።
በአውደ ጥናቱ ከተሳተፉት መካከል የውመን ኢን ኒውክሊየር ኢትዮጵያ ፕሬዝደንት አበባ ጌጡ፤ አውደ ጥናቱ በቂ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ላይ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ነው የገለጹት።
በቀጣይም በፕሮግራሙ ላይ የሴቶች አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንዲሆን በስልጠና እንዲሁም በተለያዩ አውደ ጥናቶች የማብቃት ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በአውደ ጥናቱ ጥልቅ እውቀት ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን የጨረራና ኒውክሊየር ቴክኖሎጂ የማሳወቅ እና ፈቃድ አሰጣጥ መሪ ስራ አስፈጻሚ ስሩር ከድር ናቸው።
ተጨማሪ እውቀት በመፍጠር በዘርፉ የተሰማሩትን ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።