ቀጥታ፡

በመዲናዋ የህዝብ እርካታን የሚያሳድጉ አገልግሎቶችን ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የህዝብ እርካታን የሚያሳድጉ አገልግሎቶችን ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።   

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳልጡ ስማርት የወረዳ አስተዳደር ህንጻዎችን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።    


 

ለምረቃ የበቁት የአስተዳደር ህንጻዎች በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ፣ በላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 እና ወረዳ 1 የሚገኙ ህንጻዎች ናቸው። 

ህንጻዎቹ የተለያዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በተናበበ እና በተሳለጠ መልኩ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ ሲሆን የአገልግሎት መስጫ ቢሮዎች ፣የመሰብሰቢያ አዳራሾችና የመኪና ማቆሚያዎች የተሟሉላቸው ናቸው፡፡  

ህንጻዎቹ የህጻናት ማቆያ፣ አረንጓዴ ስፍራዎችን ጨምሮ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውም በዚሁ መርሐ ግብር ላይ ተመላክቷል፡፡


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ እያደገ ለመጣው የህዝብ ፍላጎት ተመጣጣኝ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ዘመኑን የዋጁ አገልግሎቶች ተደራሽ ማድረግ ጊዜው የሚጠይቀው ነው፡፡   


 

የከተማ አስተዳደሩ ቀልጣፋና የተናበበ አገልግሎት ለመስጠት የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል ። 

ዛሬ በሶስት ቦታዎች ላይ የተመረቁት ስማርት አገልግሎት መስጫ ህንጻዎች የዚህ ጥረት ማሳያ ናቸውም ብለዋል፡፡  

አገልግሎት አሳጣጡ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ከግንባታ ባሻገር ለሰው ሃይልም ሰፊ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡


 

አገልግሎት ሰጪዎች በክህሎት እና በአመለካከት የዳበሩ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ረገድ የመዲናዋ አመራሮች  የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ዛሬ በይፋ የተመረቁት ስማርት አገልግሎት መስጫ ህንጻዎችን ደረጃ በደረጃ በሌሎች ክፍለ ከተሞችም የማስፋፋት ተግባራት እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም