ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሚናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን- የኃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሚናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን- የኃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች
ገንዳ ውኃ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሚናቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የዞኑ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
በወቅታዊ የሰላም ግንባታና ሰላምን ማጽናት ላይ የኃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችን ያሳተፈ የምክክር መድረክ ዛሬ በገንዳ ውኃ ከተማ ተካሄዷል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሀገር ሽማግሌው አቶ ሹመት ምስጋናው ፤ መንግስት ሕግ ከማስከበር ጎን ለጎን የሰላም በሮችን ክፍት አድርጎ ለሰላም ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ሰላም የሁሉም መሰረት መሆኑን አንስተው፤ ወደ ሰላም የመጡ ወገኖች መንግስት የሰጣቸውን እድል ተጠቅመው የበደሉትን ሕዝብ እንዲክሱ ለማድረግ ሚናቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
አሁን በአካባቢው የሰፈነው ሰላም እንዲመጣ ብዙ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ በአካባቢው ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
ሌላኛው ተሳታፊ ሸህ ሁሴን አህመድ በበኩላቸው፤ መንግስትና ሕዝብ እጅና ጓንት ሆነው በመስራት ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት የጀመሩትን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ለዚህም እንደ ሐይማኖት አባት ህብረተሰቡን በማስተማርና አጥፊዎችን በመገሰፅ ሰላምን ለማጠናከር እንሰራለን ያሉት የሃይማኖት አባቱ፣ ለዘላቂ ሰላም ሚናቸውን ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።
ለዘላቂ ሰላም አጥብቀው እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ አቶ ጓዴ አራጋው ናቸው። ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ እንደሀይማኖት አባት የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ እንደቆዩ አስታውሰው፤ በቀጣይም ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ በበኩላቸው፤ በአካባቢው የሰፈነው ሰላም ይበልጥ እንዲጠናከር ቅንጅታዊ ሥራው ይቀጥላል ብለዋል።
የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም ግንባታ የማይተካ ሚናቸውን በመወጣት እያበረከቱት ያለውን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉም አመልክተዋል።
በመከላከያ ሰሜን ምዕራብ ዕዝ የ504ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ቾምቤ ወርቁ፤ ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ እንደማይመጣ ገልጸው፤ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ሥራ ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ማህበረሰቡ ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ ለተገኘው ሰላም የጎላ ሚና መጫወቱን ጠቅሰው፤ ሰላሙን ለማፅናት በሚደረገው ጥረትም ሕብረተሰቡ ድጋፉን ማጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።