ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የግልፅነት መርህ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደትን እያፋጠነ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የግልፅነት መርህ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችውን ሂደት እያፋጠነ መሆኑን የዓለም ንግድ ድርጅት አክሴሽን ዲቪዥን ዳይሬክተር ማይካ ኦሺካዋ ገለጹ፡፡ 

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር ሂደት እና በተከናወኑ ስራዎች ላይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ለመፍጠር "ኢትዮጵያን በንግድ በማስተሳሰር፤ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው ፎረም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል፡፡  


 

የዓለም ንግድ ድርጅት አክሴሽን ዲቪዥን ዳይሬክተር ማይካ ኦሺካዋ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን የተቀመጡ መስፈርቶችን በፍጥነት እያካሄደች ትገኛለች ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአባልነት ሂደት 22 ዓመታትን ማስቆጠሩን አስታውሰው አሁን ላይ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት አመርቂ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን ቀጣይነት ያለው ተሳትፎ እያከናወነች መሆኑን ጠቅሰው በቴክኒክ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ የተጠናከረ የድርድር ሂደት እያካሄደች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በስድስተኛው የድርድር ሂደት ለቀረቡላት ሁሉም ጥያቄዎች በቂ ምላሽ መስጠቷ የሀገር ውስጥ የፖሊሲ ጥንካሬዎችንና ውሳኔዎችን ያመላክታል ብለዋል፡፡

በድርድር ሂደቱ ሙሉ በሙሉ በሰነድ የተደገፈ ግብዓት ማቅረቧ ለገበያ ተደራሽነት ወሳኝ መሠረት ለመጣል እንደሚያስችላት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዕቃዎችና አገልግሎቶች ዙሪያ ያቀረበችው የተመጣጠነ ዋጋ  ጠንካራ እና ተዓማኒነት ያለው መሆኑን አስር አባል ሀገራት ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም አባል ሀገራቱ በፍጥነት ወደ ዝርዝር የቴክኒክ ድርድር ለመግባት ፍላጎት እንዳላቸው ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት መቻሏን ጠቁመው ለዓለም የንግድ ድርጅት አባላት ያቀረበቻቸው የሕግ ሰነዶች 400 መድረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡


 

ይህም በሌሎች ሀገራት የድርድር ሂደት ከታዩት እጅግ ከፍተኛው ቁጥር በመሆኑ ለዓለም ንግድ ድርጅት የግልጽነት መርህ ምሳሌ ሆናለች ብለዋል።

ከድርድር ቡድኑ ሚና ባሻገርም የኢትዮጵያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ለአባልነት ሂደቱ መፋጠን ወሳኝ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን የአባልነት ጉዞ ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸው ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ ጋር የሚጣጣም ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም