የመደመር መንግስት እሳቤ ሀገር አሻጋሪ ራዕይ ያለው በመሆኑ ለተግባራዊነቱ እንተጋለን-አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግስት እሳቤ ሀገር አሻጋሪ ራዕይ ያለው በመሆኑ ለተግባራዊነቱ እንተጋለን-አመራሮች
ጎንደር ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፡- የመደመር መንግስት እሳቤ ሀገር አሻጋሪ ራዕይና ተልዕኮ ያለው በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ግንባር ቀደም በመሆን በቁርጠኝነት እንተጋለን ሲሉ የጎንደር ማዕከል ሰልጣኝ አመራሮች ተናገሩ።
ከጎንደር ከተማ አስተዳደርና ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተውጣጡ አመራሮች በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።
ከሰልጣኝ አመራሮቹ ውስጥ አቶ ነጋ አሰፋ፤ የመደመር መንግስት እሳቤዎች ብዝሀ ኢኮኖሚን በመገንባት ለብልጽግና ጉዞ መሳካት ትልቅ የኢኮኖሚ ምሰሶ ነው ብለዋል።
መንግስት ለከተሞች ልማትና እድገት መፋጠን የጀመራቸው ተግባራት በከተሞች ድህነትና ስራ አጥነት ችግር በመፍታት በኩል ታላቅ ተስፋን የፈነጠቀ እርምጃ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ሌላው ተሳታፊ አቶ ዋሲሁን ሞላ እንዳሉት፤ የመደመር መንግስት እሳቤዎች በኢትዮጵያ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ የተቀመጠውን ግብ አመራሩ በቁርጠኝነት እንዲፈጽም ምቹ የፖለቲካ አውድ የሚፈጥር ነው፡፡
ስልጠናው የነበረብንን የአስተሳሰብና የእውቀት ክፍተቶች በመሙላት በቀጣይ ሀገር አሻጋሪ የሆነውን የመደመር መንግስት እሳቤዎች ከአካባቢያችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ መተግበር እንድንችል አቅም ፈጥሮልናል ብለዋል፡፡
በቅርቡ የተፈረመው የዘላቂ ሰላም ስምምነት አዎንታዊ እርምጃ ከመሆኑም በላይ አመራሩና ሕዝቡ በቅንጅት እያከነወኑት ላለው የሰላም ግንባታ ተግባራት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
የመደመር መንግስት እሳቤዎች ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ የልማት አቅሞችና የተፈጥሮ ሀብት ጸጋዎች እንድትጠቀም ምቹ ሀገር በቀል የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያመላከተ ነው ያሉት ደግሞ አቶ አበበ ጌጡ ናቸው፡፡
ስልጠናው የአመራሩን እሳቤዎችና እይታዎች በማሳደግ በተደመረ አቅም በመፍጠርና በመፍጠን መርህ የብልፅግና ጉዞው ስኬታማ እንዲሆን አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር እንደሆነ ጠቁመው ፤ ለተግባራዊነቱም ግንባር ቀደም በመሆን በቁርጠኝነት እንደሚተጉ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ የተደረሰው የዘላቂ ሰላም ስምምነት መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ጠቁመው፤ ሰላምን የማፅናቱ ተግባር እንዲሳካ በግንባር ቀደምትነት ጠንከረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች መልካም ተሞክሮ የሚቀሰምባቸው እንደሆኑ ሰልጣኝ አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡
የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና ጥገና ስራም መንግስት ለታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃ የሰጠው ትኩረት ማሳያ እንደሆነ አመልክተው፤ የከተማ ግብርና ስራዎችም የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ድርሻቸው የላቀ መሆኑን በምልከታው መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡
አመራሮቹ በከተማው የተከናወነውን የኮሪደር ልማት፣ የከተማ ግብርና የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶችንና ኢንዱስትሪዎችን እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።