ቀጥታ፡

የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር ተጠቃሚዎችን የምግብ ሉአላዊነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ውጤት እያመጡ ነው 

ድሬዳዋ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦በድሬዳዋ አስተዳደር የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር ተጠቃሚዎችን የምግብ ሉአላዊነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ። 

የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ኢብራሂም ዩሱፍ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ለልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚ  አርሶአደሮች አበርክተዋል።


 

ከንቲባ ከድር በወቅቱ እንዳሉት፤ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር ተጠቃሚዎችን የምግብ ሉአላዊነት ለማረጋገጥና ከጥገኝነት ለማውጣት እየተሰሩ የሚገኙ ልማቶች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ናቸው።

በአስተዳደሩ የተረጂነት አስተሳሰብ እየተለወጠ መሆኑን ጠቅሰው አርሶአደሩና አርብቶአደሩ ያለውን መሬት፣ ውሃ እና ጉልበት በማቀናጀት ውጤታማ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።


 

መሬት ፆሙን እንዳያድር፣ ለውሃ ገብ የመስኖ ተጠቃሚዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግና በዓመት ሶስት ጊዜ በማምረት ከቤተሰብ አልፎ ለገበያ ማቅረብ የጀመሩ ግንባር ቀደም አርሶአደሮች እየተፈጠሩ መሆኑን አንስተዋል።

ዛሬ የተደረገው ድጋፍም የተጀመሩትን ሥራዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እና ከጥገኝነት የወጣ ማህበረሰብ ለመገንባት አጋዥ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአስተዳደሩ ምክርቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው፤ ዛሬ የተደረገው ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች ድጋፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት የመላቀቁን ጉዞ እንደሚያፋጥን ገልፀዋል።


 

ተረጂነትን ሙሉ በሙሉ የማጥፋቱ ጉዞ እንዲሳካ የሚደረገው የተቀናጀ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።

ባለፉት ዓመታት በአስተዳደሩ አራቱም ክላስተሮች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በመሸጋገር ምርትና ምርታማነት  ለማሳደግ የአነስተኛ መስኖና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በብዛትና በጥራት መከናወናቸውን የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ ናቸው።


 

አቶ ኑረዲን አክለውም፤ ዛሬ ለአርሶአደሮቹ  በ8 ሚሊዮን ብር ተገዝተው ከተሰጡት  የውሃ መሳቢያ ሞተሮች በተጨማሪ   በልማታዊ ሴፍትኔት መርሃግብር የታቀፉ ከ7ሺህ 500 በላይ የቤተሰብ ሃላፊዎች በተለያዩ የገቢ አማራጭ ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ስልጠናና የመነሻ ገንዘብ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

በዚህ አመት መጨረሻ ከ26 ሺህ 970 በላይ የልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚዎች ራሳቸውን ችለው ከመርሃ ግብሩ እንደሚሰናበቱም አረጋግጠዋል።

ዛሬ በተካሄደው ስነስርዓት ላይ ከውሃ መሳቢያ ሞተሮች በተጨማሪ በ6 ሚሊዮን ብር የተገዙ የመስክ ስራ የደህንነት መጠበቂያ ልብስና ቁሶች ለማህበረሰብ ስራ አስተባባሪዎች መበርከቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም