በአካባቢው ያለውን አስተማማኝ ሰላም በማጽናት የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአካባቢው ያለውን አስተማማኝ ሰላም በማጽናት የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ በቅንጅት እየተሰራ ነው
ሐረር ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦በምስራቅ ኢትዮጵያ ያለውን አስተማማኝ ሰላም በማጽናት የተጀመሩ የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ፍቃዱ ፀጋዬ ገለጹ።
የምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች፣ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የፀጥታ ጥምር ግብረ ኃይል በሠላምና ፀጥታ ዙሪያ ውይይት አካሄደዋል።
የውይይቱ ዓላማም በዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች የፀጥታ አካላት የአካባቢውን ሠላም እና ፀጥታ የበለጠ አጠናክረው ለማስቀጠል ያለመ መሆኑ ታውቋል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ፍቃዱ ፀጋዬ፤ በምስራቅ ኢትዮጵያ ያለውን አስተማማኝ ሰላም በማዝለቅ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።
በተለይም አካባቢው ከፍተኛ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የሚታይበትና አሸባሪዎች ሰላምን ለማናጋት የሚጥሩበት በመሆኑ የጸጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት ሌት ከቀን ለሰላም የሚሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የጸጥታ አካላት በቅንጅትና በትብብር የሰላም ዘብ ሆነው እየሰሩ መሆኑን አንስተው የሀገር መከላከያ ሰራዊትም ሰላምን በማጽናት የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ የላቀ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የሐረሪ፣ በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ እና የምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች፣ በሶማሌ ክልል የሲቲ እና የፋፈን ዞኖች፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና የማያ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ አመራሮችና የፖሊስ ኮሚሽነሮች እንዲሁም የምስራቅ ዕዝ እና የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።