በዞኖቹ ከ27 ሺህ 200 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኖቹ ከ27 ሺህ 200 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ ነው
ደብረ ማርቆስ/ ገንዳውሃ ፤ታህሳስ 2/2018 (ኢዜአ)፡- በምሥራቅ ጎጃምና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ከ27 ሺህ 200 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ መሆኑን የየዞኖቹ ግብርና መምሪያዎች አስታወቁ።
አርሶ አደሮች፤ ቀደም ሲል ጀምሮ በበጋ ስንዴ ልማት ላይ በመሳተፍ ውጤታማ መሆናቸውንና ልማቱን ዘንድሮም ለማጠናከር ግብአት እየተጠቀሙ ወደ ተግባር መግባታቸውን ተናግረዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የመስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ ሃብታሙ ማህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በዚህም እስካሁን በተደረገ ጥረት ከ13 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ በማለሰለስ ከዚህም 7 ሺህ 500 ሄክታር በዘር መሸፈኑን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅትም 12ሺህ ሄክታር መሬት በተመሳሳይ ለማልማት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ለልማቱ በግብአትነት የሚውል ከ60 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ቀርቦ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ተናግረዋል።
8 ሺህ 200 የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሮች መቅረቡን ጠቅሰው፤ ከሚለማው መሬትም ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የመስኖና ውሃ አጠቃቀም ባለሙያ አስናቀው አራጋው እንዳሉት፤ በዞኑ 2 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እየተሰራ ነው።
በልማቱ አርሶ አደሮች፣ ባለሃብቶችና ወጣቶች እየተሳተፉ ሲሆን፤ እስካሁን ከ400 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ተችሏል ብለዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግም ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በማህበራት በኩል እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሚለማው መሬትም 80 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ የየውላ ቀበሌ አርሶ አደር አስከዚያ ምረት በሰጡት አስተያየት፤ ከግማሽ ሄክታር በላይ መሬት የበጋ ስንዴ ለማልማት በዝግጅት ላይ ነኝ ብለዋል።
ባላፉት ሦስት ዓመታት በበጋ ስንዴ ልማት በመሳተፍ የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተው፤ ልማቱን ዘንድሮም ለማጠናከር የተሻለ ግብዓት በመጠቀም የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ወደ ተግባር መግባታቸውን ተናግረዋል።
የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ጓዴነህ አንዷለም፤ ግማሽ ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፈው ዓመት አልምተው ለገበያ ካቀረቡት ምርት ተጠቃሚ እንደሆኑም አስታውሰዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ አርሶ አደር ይመር አበበ በሰጡት አስተያየት፤ በበጋ መስኖ ስንዴ ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል ማልማት እንደቻሉና የሰብሉ ቡቃያም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሌላኛው ተሳታፊ ወጣት ይበልጣል አምሳሉ በበኩሉ እንዳለው፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በመሳተፍ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ተጨማሪ ገቢ የማግኘት እቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል።
ከዚህ በፊት አካባቢው ለስንዴ ልማት አይሆንም የሚል እምነት ነበረን ያለው ወጣቱ ፤ ሆኖም ባለፉት ዓመታት አልምተው ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች በማየት ወደ ልማቱ መግባቱን ገልጿል።
ከመደበኛ መስኖ በተጨማሪ በስንዴ ዘር የሸፈንኩት ግማሽ ሄክታር መሬት የቡቃያው ሁኔታ በጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ሙሐመድ ስጦታው ናቸው።
ካለሙት መሬትም የተሻለ ምርት በመሰብሰብ ተጠቃሚ ለመሆን በቂ ግብዓት መጠቀማቸውን ገልጸዋል።