ፋይዳ መታወቂያ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው -ተቋማት - ኢዜአ አማርኛ
ፋይዳ መታወቂያ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው -ተቋማት
ሐረር፤ ታህሳስ 2/2018 (ኢዜአ) ፡- ፋይዳ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን በሐረሪ ክልል የሚገኙ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ገለጹ።
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ ማድረግ አንዱ ነው።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ማንኛውም አገልግሎት ፈላጊ ዜጋ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያን እንዲይዝ መንግስት የተለያዩ አማራጮችን መዘርጋቱ የዚሁ ጥረት አካል ነው።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሐረሪ ክልል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
በሐረሪ ክልል ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ የውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ባለሙያ አቶ ዘኪ አብዱልማሊክ ፤ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ መደረጉ በተለይም ከዚህ በፊት በመታወቂያ ረገድ ይስተዋል የነበረው ማጭበርበር ችግር ማቃለሉን ገልጸዋል።
ፋይዳ ከሲስተም ጋር የተሳሰረ በመሆኑ አንድ ሰው በአንድ ማንነትና በአንድ መታወቂያብቻ እንዲገለገል አድርጓል፣ የነበሩ ብልሹ አሠራሮችንም ሙሉ በሙሉ እንዳሰቀረ ተናግረዋል።
የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ሁሉንም ዜጎች ተደራሽ ያደረገ ነው ያሉት ደግሞ በሐረሪ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል ኢትዮ- ፖስታ በሚሰጠው አገልግሎት የካውንተር ባለሙያ አቶ አብዲሳ ተካ ናቸው።
በተጨማሪም ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ለግለሰብም ሆነ ለሀገር ደሕንነት የጎላ ፋይዳ እንዳለውና እንደ ሀገር ለተጀመረው የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች አንዱ ማሳያ መሆኑንም አክለዋል።
ሌላው በሐረሪ መሶብ የአንድ ማዕከል ኢትዮ-ፖስታ በሚሰጠው አገልግሎት የካውንተር ባለሙያ ዮሐንስ እስቂያስ በበኩላቸው፤ ፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ተቋማት ያለ ልዩነት አገልግሎት እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ሲል ተናግረዋል።
በአገልግሎት ሰጪ እና ተቀባዩ መካከልም መተማመን እንዲፈጠር ያስቻለ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የሐረሪ ክልል ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ኃላፊና የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ አስተባባሪ አቶ አርሰላን አብዲ ፤ በክልሉ እስካሁን 263ሺህ ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ ተመዝግበው መውሰዳቸውንና ይህም ከእቅዱ በላይ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም በክልሉ የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ያልወሰዱ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም እንደ ሀገር ለተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን፣ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓት ግንባታ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
የሀገር እና ዜጎችን ደሕንነትን በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ አአስተዋጽኦ አለው ያሉት ሃላፊው፤ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መያዝ እንደሚጠቅማቸው በመረዳት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።