ቀጥታ፡

በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት የሀገርና ሕዝብን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የሰላም አማራጭ ሊቀበሉ ይገባል - የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት የሀገርና ሕዝብን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የሰላም አማራጭ ሊቀበሉ እንደማገባ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች አስታወቁ።

የአማራ ሕዝብ በውክልና ጦርነት እንዲቆይ የሚሹ የጥፋት ተልዕኮዎችን በመተው ትክክለኛውን የሰላም ስምምነት አማራጭ መቀበላቸውንም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።


 

በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ምክትል የፖለቲካ መምሪያ ኃላፊና የወሎ ቤተ-አማራ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ እያሡ አበራ፥ የአማራን ህዝብ ጥያቄ በትጥቅ ትግል እናስከብራለን በሚል በጫካ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል መንግስትና በሕዝባዊ ድርጅቱ የተፈረመው የሰላም ስምምነትም የአማራን ሕዝብ ክብርና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባከበረ መንገድ የተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።

በተፈረመው የሰላም ስምምነትም በዘፈቀደ የተመራ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው መንገድ የተፈጸመ መሆኑንም አንስቷል።

የአማራ ሕዝብ ከዚህ በላይ ጦርነትን የመሸከም አቅም የለውም፥ ሌሎች በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላትም የሕዝብና የሀገርን ጥቅምና ክብር በሚያስከብር አግባብ የሰላም አማራጭን መቀበል አለባቸው ብለዋል።

በዚህም ለሕዝብ የሚበጅ ትክክለኛ የንግግር ውሳኔን በማሳለፍ የሰላም አማራጭ መምረጣቸውን አስረድተዋል።

በቀጣይም የሀገርና ሕዝብን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት በማስጠበቅ ከክልሉና ፌደራል መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ከዚህ ውጭ ያለ አካሄድ የሽፍትነት ተግባር ነው፥ ዝና እና የግል ጥቅምን በማስቀደም የሚደረግ ጽንፍ የረገጠ የብሔርተኝነት ትግል የትም አያደርስም ብለዋል።


 

በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የፋይናንስ ኃላፊ ከፋለ አለሙ፥ ከዓመታት በፊት ጀምሮ ዘላቂ ሰላምን ለማውረድ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ንግግር መደረጉን አስታውሰዋል።

በዚህም የተደረጉ ንግግሮች ፍሬ አፍርተው የዘላቂ ሰላም ስምምነት መፈረሙም ሕዝብን፣ የድርጅቱን አመራርና የሠራዊት አባላት ያስደሰተ መሆኑን ገልጸዋል።

ከቀድሞው ሕወሓት፣ ሻዕቢያ እና ግብጽ ጋር የሚደረግ የጥፋት ተልዕኮም ለአማራ ሕዝብም ሆነ ኢትዮጵያ የሚጠቅም ባለመሆኑ የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን ተናግረዋል።

መርህ የለሽ የትጥቅ ትግል ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው በማስቀረት ጫና እያሳደረ በመሆኑ ቀሪ በጫካ የሚገኙ የፋኖ አደረጃጀቶችም የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።


 

በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የወሎ ቤተ-አማራ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የሕዝብ አስተዳደርና ማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ ግርማ እጅጋየሁ፥ በትጥቅ ትግል በነበሩባቸው ጥቂት ዓመታት የአማራን ሕዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉስቁልና እንዲያስተናግድ አድርጓል ብለዋል።

በዚህም ትክክለኛውን የሰላም አማራጭ በመከተል የተሄደበት የተሳሳተ የውክልና ጦርነት በመተው የሰላም ስምምነት መምረጣቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በቀድሞው ሕወሓት በሚያደርገው ድጋፍ አማራ እርስ በዕርሱ ዋጋ እየከፈለ መሆኑን በመገንዘብ ሌሎች በጫካ የሚገኙ አደረጃጀቶች የሰላም አማራጭ መቀበል እንደሚኖርባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመግለጫው ላይ ሌሎች የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም