በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ውጤታማ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ውጤታማ ናቸው
አዳማ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የዘንድሮውን የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራን ስኬታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ ሙያተኞችና የስራ ኃላፊዎችን ያሳተፈ የቅድመ ዝግጅት መድረክ በአዳማ ገልመ አባገዳ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
የቢሮው ኃላፊ ጌቱ ገመቹ በዚህ ወቅት እንደገለፁት ዘንድሮ የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ በትኩረት ይከናወናል።
በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገልፀው በዚህም የመሬት መራቆት፣ የአፈር መሸርሸር፣ የጎርፍና የድርቅ ስጋት መቀነሱን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም፣ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ ዓምና የእርከን ማሰር፣ የአፈርና ውሃ ዕቀባ፣ የተፋሰስና በአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራም የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ተግባር መከናወኑን አስረድተዋል።
ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎችም የከርሰ እና ገፀ ምድር የውሃ ሀብት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው የደረቁ ወንዞች፤ ጅረቶችና ሃይቆች መመለሳቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የበጋ መስኖ ስንዴን በበቂ የውሃ አቅርቦት ማልማት መቻሉን ገልጸው ለዓሣ ዕርባታና ለመጠጥ አገልግሎቶች እየዋሉ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተመሳሳይም ከሰውና እንስሳት ንኪኪ ነፃ ሆኖ ያገገመ መሬትን የደን ሀብቱን በመጠበቅ ለስራ ዕድል ፈጠራ ከማዋል ባለፈ ለንብ ማነብ ተግባር እየዋለ ይገኛል ብለዋል።
በዘርፉ የተገኘውን ውጤት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ዘንድሮ የአፈርና ውሃ ዕቀባና የተፋሰስ ልማት ስራውን ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ለዚህም አምስት ሺህ 930 ተፋሰሶች መለየታቸውን ገልፀው በአፈርና ውሃ እቀባውና በተፋሰስ ልማት ስራው ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ሚሊየን ህዝብን ለማሳተፍ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።