የኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር በምሳሌነት የሚወሰድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር በምሳሌነት የሚወሰድ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር በምሳሌነት የሚወሰድ መሆኑን የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ዋና ጸኃፊ ዋምኬሌ ሜኔ ገለጹ፡፡
የአፍሪካ ሀገራትን የዕርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ ለማሳለጥ የጋራ መገበያያ ገንዘብን ሥራ ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ሁለተኛው የኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ዓመታዊ ጉበዔ ተካሂዷል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ዋና ጸኃፊ ዋምኬሌ ሜኔ በጉባዔው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በአፍሪካ በየዓመቱ የሚፈጸመውን የአምስት ቢሊዮን ዶላር የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ በማሳለጥም የአህጉሪቱን የጋራ መገበያያ ገንዘብ ግብ ለማሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የአህጉሪቱ የንግድ ልውውጥ በሶስተኛ ወገን ገንዘብ ይፈጸማል ያሉት ዋና ጸኃፊው፤ ይህም አፍሪካውያን ለአላስፈላጊ ወጪ እንዲጋለጡ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሀገራትን የዕርስ በዕርስ የንግድ ልውውጥ ወጪ ቆጣቢ፣ ዘመናዊና ፈጣን ለማድረግም አህጉራዊ የጋራ መጠቀሚያ ገንዘብን በሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ አስረድተዋል።
በአህጉሪቱ የንግድ ልውውጥም ሀገራት በየራሳቸው ገንዘብ ግብይት የሚፈጽሙበትን ቀልጣፋ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባም አብራርተዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናም የአፍሪካ ሀገራትን የንግድ ልውውጥ የሚያሳልጥ የአሰራር ሥርዓት ምክረ ሃሳቦችን በመፍጠር የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዋና ጸሃፊው ኢትዮጵያ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስኬታማ ስራ እየሰራች መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዲጂታል ክፍያ ስርዓት ፍትሐዊ የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር በምሳሌነት የሚወሰድ ሥራ እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።