ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በ2026 የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለማድረግ ግብ ተይዞ ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን በ2026 የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለማድረግ ግብ ተይዞ ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር ሂደት እና በተከናወኑ ስራዎች ላይ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ለመፍጠር "ኢትዮጵያን በንግድ በማስተሳሰር፤ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር " በሚል መሪ ሐሳብ ፎረም እየተካሄደ ይገኛል።


 

ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ስታቅድ የኢኮኖሚ ዕድገቷን ለማስቀጠል፣ ኢንቨስትመንትን ለመሣብ ብሎም ሌሎች በርካታ ግቦችን በማንገብ ነው።

የዓለም ንግድ ድርጅት የዓለምን ንግድ 98 በመቶ የሚሸፍኑ 166 አባል ሀገራት በውስጡ የያዘ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ለአባልነት ያስገባችው ማመልከቻ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ድርድር መግባቷን ተናግረዋል።

ለዚህም የድርድር ቡድን መደራጀቱን ጠቁመው፤ እስካሁንም ስድስት ዙር ድርድሮች ማድረጓን ገልጸዋል።

እስካሁን በተደረጉ የባለብዙ ወገን ድርድሮች ከ1ሺህ 50 በላይ ጥያቄዎች በአጥጋቢ ሁኔታ ምላሽ መስጠቷን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ አባል ለመሆን በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗንም አክለዋል።

የዓለም የንግድ ድርጅት አባል መሆን ደህንነቱ የተረጋገጠ የንግድ ምህዳር ለመፍጠርና የኢትዮጵያን ምርቶች ተፈላጊነት ያሳድጋልም ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያን በ2026 የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለማድረግ ግብ ተይዞ ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህም የኢኮኖሚ አቅምን ለማሳደግና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ገልጸው፤ ለዚህ ስኬትም የባለድርሻ አካላት ድርሻ ወሣኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም