ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ሰላምን በማፅናት ልማትን ለማረጋገጥ ወጣቱ የሚያደርገውን ተሳትፎ ማጠናከር ይጠበቅበታል

ደሴ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰላምን በማፅናት ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ወጣቱ በተደራጀ አግባብ የሚያደርገውን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚጠበቅበት ተመላከተ።

የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ከወጣቶች ጋር በደሴ ከተማ እየተወያዩ ነው።

በመድረኩ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ እንዳመለከቱት፤ የክልሉን ሰላም በማፅናት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን፣ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል፣ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ለማልማት እየተሰራ ነው።


 

ይህም የማዕድን ሀብቶችን ጭምር ወደ ልማት በመቀየር የሕብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ለክልሉ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና መረጋገጥ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተው ወጣቱ ጉልበቱን፣ እውቀቱን፣ አቅሙንና ጊዜውን ተጠቅሞ የተጀመሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ዳር እንዲደርሱ ተሳትፎውን በተደራጀ አግባብ በማጠናከር የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት ለውይይትና ለንግግር አሁንም በሩ ክፍት መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ ጎን ለጎን ሕግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፣ ሕብረተሰቡን በማስተባበር በከተማው የሰፈነውን ሰላም በማስጠበቅ አስደናቂ የልማት ስራዎችን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።

በኮሪደር ልማት፣ በመንገድ፣ በሥራ እድል መፍጠሪያ ሸድ፣ በሌማት ትሩፋትና በሌሎችም አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።

በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ለሕብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት በመስጠት የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየተቃለሉ መምጣታቸውን አንስተዋል።


 

ለዚህም ወጣቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመው፤ ሰላሙን ዘላቂ በማድረግ ለማፅናት በሚደረገው ጥረትም ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጠልም አመልክተዋል።

በመድረኩ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም