ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅና የወል ትርክት ግንባታ ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅና የወል ትርክት ግንባታ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ ገለጹ።

መገናኛ ብዙኃን ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማጎልበት፣ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ ማህበራዊ ንቃትንና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ በመረጃ ተደራሽነትና በማስተማር ሰፊ ሚና እንዳላቸው  ይታወቃል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ባህልን የሚያጎለብቱ፣ አንድነትን የሚያጠናክሩና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የሀሳብ ልዕልና እና ብዝኃነት ወሳኝ  ነው ያሉት ሰብሳቢው፥ ለዚህ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃንን ሚና ለማጎልበት ምቹ የአሠራር ምህዳር መፈጠሩን ተናግረዋል።

ሆኖም የሚተላለፉት መረጃዎች የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የማይጎዱ፣ የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት የማይሸረሽሩ መሆን አለባቸው ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን በሚያስተላልፏቸው ይዘቶች ላይ ልዩነቶች መኖራቸው አይቀሬ መሆኑን ገልጸው፥ የሚሠራጩ መልዕክቶች የግጭት መንስኤ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያውያን ለሀገር ክብርና ብሔራዊ ጥቅም በአንድነትና በአይበገሬነት እንደሚሰለፉ የዓድዋ ድል ዘመን አይሽሬ ምልክት ነው ያሉት ሰብሳቢው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች ቢኖሩም ሀገርን ማስቀደም ይገባል ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃንም ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅና በወል ትርክት ግንባታ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም