መልካምነት ይከፍላል..!!! - ኢዜአ አማርኛ
መልካምነት ይከፍላል..!!!
መልካምነት ይከፍላል...!!!
በማስረሻ ሀብታሙ (ኢዜአ-ወላይታ ሶዶ ቅርንጫፍ)
መልካም ስነ ምግባርና ባህሪ ከራስ ባለፈ ቤተሰብን ያኮራል፤ ከዚህ ከፍ ሲልም ለማህበረሰብ ግንባታና ለሀገር የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው። ሌብነትና ሙስናን ለመከላከልም እንዲሁ አስተዋጾ አለው።
በመልካም ስነምግባር ታንጾ ያደገ ሰው በላቡና በወዙ ጥሮ ግሮ ያፈራውን እንጂ የሌሎች የሆነን ሀብትና ንብረት አይመኝም።
ዛሬ የራሱ ያልሆነውን ንብረት በሀሰት ምሎና ተገዝቶ ለመውሰድና ለመክበር የሚጥር ሰው በበዛበት በዚህ ዘመን ላይ ወድቆ ያገኙትን ንብረት ለባለቤቱ ለመመለስ "ገንዘብ የጣለ" እያለ በአደባባይ ባለቤቱን የሚያፈላለግ ሰው ሲገጥም ግርምትን ከማጫር ባለፈ እንዲህ አይነት ሰውም አለ ወይ? ያስብላል።
ነገሩ የተከሰተው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ገረሴ ዙሪያ ወረዳ ኮሻሌ ቀበሌ ነው። በአካባቢው ባህልና እምነት የሰው ገንዘብም ሆነ ንብረት ያለአግባብ መውሰድ "ጎሜ" ወይም እንደ "ሀጥያት" ተደርጎ ይቆጠራል።
በኮሻሌ ቀበሌ ተወልደው ያደጉት አርሶ አደር ሴዳ ጋርዜ በዚህ ባህልና እምነት ውስጥ ያደጉ ቢሆንም በቤተሰባቸው በመልካም ስነ ምግባር ታንጸው ማደጋቸው አሁን ላላቸው ታማኝነትና ቅንነት ትልቁን ድርሻ ይይዛል።
አርሶ አደሩ ታማኝነታቸውን በተግባር ጭምር በማሳየታቸው ከመንግስት ጭምር እውቅና ተችሯቸዋል። ነገሩ እንዲህ ነው አንድ ቀን ገበያ ውለው ሲመለሱ በመንገዳቸው ላይ ተጠቅልሎ የታሰረ ነገር ይመለከታሉ።
መሬት ወድቆ ያገኙት ነገር እስሩን ፈትው ሲያዩ በርከት ያለ የገንዘብ ኖት ነው። ለማመን እያቃታቸው ገንዘቡን መቁጠር ጀመሩ። በላስቲክ የተጠቀለለው ብር 30 ሺህ ነበር። የራሳቸው ያልሆነውን ገንዘብ ይዞ ወደ ቤት መግባት የህሊና እዳ መስሎ ስለታያቸው አማራጭ ያሉትን አደረጉ፡፡
የገንዘቡ ትክክለኛ ባለቤት ከተገኘ በሚል "ገንዘብ የጠፋበት! ገንዘብ የጠፋበት" እያሉ በአደባባይ ጽምጻቸውን ከፍ አድርገው መጠየቅ ጀመሩ። የሰማቸው ሁሉ ግራ ስለተጋባ ቀረብ ብሎ ሊጠይቃቸው ይቅርና ጤነኛ ሰውም አድርጎ አላያቸውም።
የገንዘቡ ባለቤት እኔ ነኝ የሚል ትክክለኛ ሰውም ባለመገኘቱ ልፋታቸው ድካም ብቻ ሆነ። የያዙትን 30 ሺህ ብር ይዘው ወደ ቤታቸው ለመሄድ ተገደዱ።
በአካባቢው የገበያ ቀን በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ነው። እናም የገንዘቡን ባለቤት ለማግኘት እስከ ሳምንት ድረስ መቆየት ግድ ሆኖባቸው። ባለቤቱ ይገኛል ወይስ አይገኝም በሚል ሀሳብ ሳምንቱን አሳለፉ።
ቀጣይ የገበያ ቀን ሲደርስም ገንዘቡን እንጨት ላይ አስረው በማንጠልጠል "ገንዘብ የጠፋበት! ገንዘብ የጠፋበት" አያሉ በገበያ ስፍራ በመዘዋወር ዳግም የጠፋበትን ሰው ማፈላለግ ጀመሩ።
ገንዘቡ የእኔ ነው፤ ጠፍቶብኛል እያለ የሚመጣ ሰው ቢበዛም ትክክለኛውን የገንዘብ መጠንና ምልክቱን የሚጠራ ሰው አለመኖሩ ግን ፍለጋቸውን አድካሚ አድርጎታል።
የገንዘቡን ባለቤት አግኝተው እስኪያስረክቡ ድረስ ተስፋ አልቆረጡም፤ “ገንዘብ የጠፋበት፣ ገንዘብ የጠፋበት...” እያሉ ገበያውን ከዳር ዳር ዞሩ።
የኋላ ኋላ ግን ድካማቸው በከንቱ አልቀረም። በስተመጨረሻ ትክክለኛውን የገንዘብ መጠን ከእነምልክቱ እና ቦታው የሚናገር አንድ ግለሰብ ተገኘ።
ከገንዘቡ ባለቤት ጋር ከተወያዩ በኋላ ገንዘቡ ወድቆ ወዳገኙበት ስፍራ ይዘው በመሄድ የያዙትን ገንዘብ መሬት ላይ ጥለው ራሱ ባለቤቱ ምሎ እንዲያነሳ ያደርጋሉ። በእዚህ ሁኔታ ወደቆ ያገኙትን ገንዘብ በታማኝነት ያስረከቡት አቶ ሴዳ ለዚህ መልካም ተግባራቸው ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በቅርቡ እውቅና ተችሯቸዋል።
የእሳቸው መልካም ተግባር መረጃ የደረሰው ኮሚሽኑም የአርሶ አደሩን አርአያነት ለሌላው ለማስተማር አፈላልጎ ያገኛቸዋል፡፡ ህዳር 26 ቀን 2018 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ ከተማ 22ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀንን ሲያከብር በማጠቃለያው ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ በተገኙበት የእውቅና ምስክር ወረቀትና የ15 ሺህ ብር ስጦታ አበርክቶላቸዋል፡፡
የክልሉ ስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የሙስናና ብልሹ አሰራር መከላከል ዘርፍ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አብደላ ከቤተሰብ ጀምሮ በትምህርት ቤቶች በዜጎች ስነ ምግባር ላይ አበክሮ መስራት እንዲህ ያሉ ዜጎችን በብዛት ለማፍራት የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት። ታማኝ የሆኑ ሰዎች ሲበራከቱ ደግሞ ሀገርና ህዝብን የሚጎዳውን ሙስና ለመከላከል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል፡
እንደ አርሶ አደር ሴዳ ጋርዜ በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ የሚገነባው ከቤት ጀምሮ በሚሰራ ሥራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ኮሚሽኑ ትውልድን በስነ-ምግባር ለማነጽ የጀመረውን ስራ ለማጠናከር በሚሰራው ሥራ እንደ አርሶ አደሩ ያሉ ታማኞች ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የተቋቋመው የጸረ ሙስና ግብረ ኃይልም በጸረ ሙስና ትግሉ ላይ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ህብረተሰቡም ታማኝነትን ባህሉ ከማድረግ ባለፈ የጸረ ሙስና ትግሉን በመደገፍ ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣም ነው ያሳሰቡት። የአርሶ አደር ሴዳ ጋርዜ መልካም ተግባርና ታማኝነትም ለብዙዎች ምሳሌ ይሆናል።
በተለይ ያለፉበትን ለማግኘትና በአቋራጭ ለመክበር የሚሯሯጡ ሰዎች ከእሳቸው መልካም ተግባር ሊማሩ ይገባል። የሰው ሀብት ወስዶ ከመክበር ይልቅ በታማኝነት ከምናቆየው ንጹህ ህሊና ይበልጥ አትራፊ እንሆናለን። ለሰዎች መልካም መስራት ክብርና ዋጋ የሚያሰጥ መሆኑንም የእኚህ አርሶ አደሩ ተሞክሮ ያሳያልና እንደእሳቸው ለሰራነው መልካም ተግባር ዋጋ እንዲከፈለን ታማኝነትን የህይወታችን መርህ ማድረግ አለብን። መልካምነት ቢቆይም እንኳ በራሱ ይከፍላልና።