የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ-ግብር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በተግባር እያገዘ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ-ግብር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በተግባር እያገዘ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የከርሰ ምድር የውሃ አቅምን በማጎልበት የመስኖ እርሻዎች እንዲስፋፉ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ተግባራዊ የተደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል፡፡
መርኃ-ግብሩ ለመጪው ትውልድ ተስፋ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለውንም ትውልድ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ሲሆን በስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ የራሱን ጉልህ ሚና እየተወጣ ነው፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ በብራዚል ቤለም በተካሄደው የዓለም የአየር ንብረት (COP-30) ጉባኤ ላይ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት (COP-32) ጉባኤን እንድታስተናግድ መመረጧ ይታወቃል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈጻሚ እና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የብሄራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ጸሃፊ ፋኑሴ መኮንን፤ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እያደረገች ላለችው ጥረት ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን አርባ በመቶ የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
አረንጓዴ አሻራ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስና ለምነትን በመጨመር የግብርና ምርታማነት እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
የከርሰ ምድር የውሃ አቅምን በማሳደግ የመስኖ እርሻዎች እንዲስፋፉም የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ለምግብነት አገልግሎት የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ጨምሮ ሌሎች ችግኞች በስፋት የተተከሉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ እነዚህም ለቤተሰብ የገቢ ምንጭና ለሥርዓተ ምግብ መሻሻልም ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን ጠቅሰዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር የተተከሉ ችግኞች ደን በመሆን ለማር ምርት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የንብ አናቢዎችን ተጠቃሚነት እያሳደጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በበርካታ ዘርፎች ሰፊ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር በተለይም የወጣቶችንና የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያሳደገ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑና የተራቆቱ አካባቢዎች ወደ ምርታማነት እንዲለወጡ በማድረግ ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ የራሱን አስተዋጾኦ እያበረከተ መሆኑን አመላክተዋል፡፡