በተጠባቂው ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ ሪያል ማድሪድን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በተጠባቂው ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ ሪያል ማድሪድን አሸነፈ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሊግ ሻምፒዮንስ ሊግ ተጠባቂ መርሃ ግብ ማንችስተር ሲቲ ሪያል ማድሪድን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ማምሻውን በሳንቲያጎ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኒኮ ኦራይሊ በጨዋታ እና አርሊንግ ሃላንድ በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ሮድሪጎ ለሪያል ማድሪድ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በጨዋታው ላይ ማንችስተር ሲቲ በመጀመሪያው አጋማሽ እና ሪያል ማድሪድ በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ ወስደው ተጫውተዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ማንችስተር ሲቲ በ13 ነጥብ ደረጃውን ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል።
የ15 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሪያል ማድሪድ በ12 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
አርሊንግ ሃላንድ በሻምፒዮንስ ሊግ በ50 ጨዋታዎች 51 ግቦችን ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋች በመሆን አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።
በሌላኛው መርሃ ግብር አርሰናል ክለብ ብሩዥን 3 ለ 0 አሸንፏል።
በጃን ብሬይዴል ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኖኒ ማዱዌኬ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ጋብርኤል ማርቲኔሊ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
አርሰናል በ18 ነጥብ መሪነቱን አጠናክሯል። መድፈኞቹ በሻምፒዮንስ ሊግ ሁሉንም ጨዋታ ማሸነፍ ችለዋል።
ክለብ ብሩዥ በአራት ነጥብ 31ኛ ደረጃን ይዟል።
የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ ከአትሌቲኮ ቢልባኦ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።
ጁቬንቱስ በጆናታን ዴቪድ እና ዌስተን ማኬኒ ግቦች ፓፎስን 2 ለ ዐ አሸንፏል።
ቤኔፊካ ናፖሊን 2 ለ 0 አሸንፏል። ባየር ሌቨርኩሰን ከኒውካስትል ዩናይትድ እና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከቦዶ ግሊምት በተመሳሳይ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።
ዛሬ አስቀድመው በተደረጉ ጨዋታዎች አያክስ ካራባግን 4 ለ 2፣ ኮፐንሃገን ቪያሪያልን 3 ለ 2 አሸንፈዋል።