የፌዴራል መንግስት በክልሉ እያከናወናቸው የሚገኙ ፕሮጀክቶች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው- ሌተናል ጀኔራል ታደሰ ወረደ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል መንግስት በክልሉ እያከናወናቸው የሚገኙ ፕሮጀክቶች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው- ሌተናል ጀኔራል ታደሰ ወረደ
መቀሌ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፦ የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል እያከናወናቸው የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌተናል ጀኔራል ታደሰ ወረደ ገለጸ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ፤ የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ በመቀሌ ከተማ ዳርቻ ላይ በ2 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ ለሚገነባ የፍሳሽ ማጣሪያና ማስወገጃ ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በትግራይ ክልል ከውሃና ሳኒቴሽን ጋር የተያያዙ የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑም ተመላክቷል።
በዚህ ወቅት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌተናል ጀኔራል ታደሰ ወረደ ፤ የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል እያከናወናቸው የሚገኙት የልማት ፕሮጀክቶች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን አረጋግጠዋል።
መሰል የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
በመቀሌ ተገኝተው ለፕሮጀክቱ የመሰረተ ደንጋይ ያስቀመጡት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ፤ የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል ለማህበራዊ አገልግሎት የሚውሉ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ማከናወኑን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ በዛሬው ዕለት በመቀሌ ከተማ ዳርቻ ላይ የሚገነባ የፍሳሽ ማስወገጃና ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ አስጀምሯል ብለዋል።
ይኸው የፍሳሽ ማጣሪያና ማስወገጃ ፕሮጀክትም በመቀሌ ከተማ ዳርቻ ላይ በ2 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የከተማው የፍሳሽ ማጣሪያና ማስወገጃ ፕሮጀክትም በአካባቢው ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በመስኖ ልማት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱን በተቀመጠለት ጊዜና ጥራት ለማጠናቀቅም ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
በክልሉ በአምስት ከተሞች የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት የሚሰጡ ፕሮጀክቶችን ሚኒስቴሩ እያከናወነ መሆኑንም አንስተዋል።
ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ ከዚህ ቀደምም በከተማዋ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ቤቶችን በመገንባት ማስረከባቸው ይታወሳል።
በእንደርታ ወረዳ የማይ ዓለም ገጠር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ቄስ ገብረኪዳን ታደሰ ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር በመስኖ ልማቱ በመጠቀም ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት እናግዛለን ብለዋል።
ወይዘሮ ለተመሰቀል ሀዱሽ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ ለልጆቻችን ተጨማሪ የሥራ ዕድልን ይፈጥራል ብለን እንጠብቃለን ብለዋል።