ቀጥታ፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በትብብር በመስራት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቷል

ወራቤ፤ ታህሳስ 1/2018 (ኢዜአ):-የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተልዕኮ ተለይተው በትብብርና በቅንጅት በመስራት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ትኩረት መሰጠቱን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢትዮጵያ ኮምፕሬሄንሲቭ ዩኒቨርሲቲዎች ማህበር 2ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በወራቤ ዩኒቨርሲቲ አካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የትምህርት ሚኒስትር ተወካይና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አገልግሎት ዴስክ ኃላፊ እዮብ አየነው (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ ሚኒስቴሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በተልዕኮ በመለየት ወደ ተግባር አስገብቷል፡፡

በዚህም ተቋማቱ በምርምር፣ በተግባር፣ በአፕላይድ እና በኮምፕሬሄንሲቭ ደረጃ ተለይተው የመማር ማስተማር ስራቸውን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የአካባቢያቸውን ፀጋ ተጠቅመው ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ትኩረት መሰጠቱንና የዚህ ጉባኤ ዋና ዓላማም ይህንን ተፈፃሚ ማድረግ መሆኑን አመልክተዋል።

ተቋማቱ በየተሰጣቸው ተልዕኮ ተቀናጅተው በትብብር በመስራት ለትምህርት ጥራት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ ሚኒስቴሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡


 

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የኮምፕሬሄንሲቭ ዩኒቨርሲቲዎች ማህበር ሰብሳቢ ድሪባ ኢቲቻ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የመማር ማስተማር ስራውን በላቀ መልኩ ለማከናወን በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑንና ማህበሩም ለእዚህ መቋቋሙን ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ያላቸውን አቅም ተጠቅመው በትብብር በመስራት በሀገራዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ተጨባጭ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማህበሩ  ይሰራል ብለዋል፡፡

በዚህም በመማር ማስተማር ሥራ፣ በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት ሌሎች ዘርፎች ላይ በቅንጅት በመስራት ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ትኩረት መደረጉን ነው ያስረዱት። 

የቀብሪደሀር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አብድልፈታ አህመድ ጠቅላላ ጉባኤው በትብብርና በቅንጅት በመስራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለን ውስን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር ስራው ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት የተሰጠውን ተልዕኮ በመወጣት ላይ መሆኑንም አንስተዋል።

ኮምፕሬሄንሲቭ ዩኒቨርሲቲዎች በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት የበቁ ዜጎችን ማፍራት ተልዕኮ እንደተሰጣቸው የተናገሩት ደግሞ የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ቶፊቅ ጀማል (ዶ/ር) ናቸው፡፡


 

ዩኒቨርሲቲው በምርምር የተገኘና ቀደም ሲል በአካባቢው ያልተለመደ የተልባ ዝርያን ጨምሮ የኦቾሎኒ ሰብሎችን በአካባቢው እንዲላመድ በማድረግ ከሀገር ባለፈ ለኤክስፖርት ምርት አስተዋጾ ማድረጉንም አንስተዋል።

የማህበሩ መቋቋም አንዱ ከሌላው እንዲማርና ከሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተሞክሮዎችን በማስፋት እንደሀገር በተለያዩ ዘርፎች የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡ 

በጠቅላላ ጉባኤው በትምህርት ሚኒስቴር ኮምፕሬሄንሲቭ በሚል የተለዩት የ21 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም