ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረዋል

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 1/ 2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመቀነስ እና በሁሉም ዘርፎች ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ ስራዎች መጠናከራቸውን የክልሉ ሴቶችና የህፃናት ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

በኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ የሚዘጋጀው 'ጉሚ በልበሎሚ' የተሰኘ የውይይት መርሃ ግብር ላይ የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ እና የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ሀላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።

ቢሮው በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ በክልሉ 16 ዞኖች እና 14 ከተሞች ያካሄደውን የዳሰሳ ጥናት ለውይይቱ መነሻ አቅርቧል።

በዳሰሳ ጥናቱ መሰረት፣ በተለይም ከለውጡ ወዲህ በክልሉ ሴቶችና ህፃናት መብቶችን ለመጠበቅ በተሰሩ ስራዎች ላይ ጥሩ መሻሻሎች መታየታቸው የተመለከተ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ችግሩ አሁንም እየተስተዋለ መሆኑ ተጠቅሷል።

በተለይም በእነዚህ ወንጀሎች ላይ በቀበሌና በወረዳ ደረጃ በሚገኙ የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑም ተነስቷል።

የደሰሳ ጥናቱን አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ሴቶችና የህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መብራት ባጫ፣ በክልሉ የሴቶችና ህፃናት መብቶችን ለመጠበቅ እና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም ከለውጡ ወዲህ መንግስት የሴቶችንና የህፃናትን መብቶች ለመጠበቅና በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመቀነስ ሴቶችን የማብቃት፣ ግንዛቤ የመፍጠር እንዲሁም ወንጀል ፈጻሚዎችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ቢሮው የሴቶችንና ህፃናትን መብቶች ለመጠበቅ፣ በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለመቀነስ እና ለተጎጂዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አክለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የማህበረሰብ ተሳትፎ አስፈላጊ በመሆኑ ማህበረሰቡን በማሳተፍ ይህንን ችግር ለመግታት ተከታታይ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቢሮ የምርመራ፣ ክትትል የስራ ሂደት ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ዋንዳፍራሽ በበኩላቸው፥ በክልሉ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ጉድለቶችን ለማረም በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህ ሂደት ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸውም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም