ቀጥታ፡

በክልሉ የሚገኙ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች የተገልጋዩን ጊዜና ወጪ በመቆጠብ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው 

ባሕር ዳር፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የሚገኙ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች የመደበኛ ፍትሕ ስርዓቱን ስራ ከማቃለል ባለፈ የተገልጋዩን ጊዜና ወጪ በመቆጠብ ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አለምአንተ አግደው ገለጹ።

በአማራ ክልል ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን ስራ የሚያሳልጥ መመሪያ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግም አቶ አለምአንተ አግደው ተናግረዋል።

በክልሉ የባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ማስተግበሪያ ጥናት፣ ትግበራ ዕቅድ እና ዕወቅና መስጫ መመሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባሕርዳር ከተማ ውይይት ተደርጓል። 


 

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አለምአንተ አግደው እንዳመለከቱት፤ በክልሉ በርካታ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች አሉ።

በዚህም የየአካባቢው ሕብረተሰብ እንደየነባራዊ ሁኔታው ግጭቶች ሲፈታባቸው የነበረ ቢሆንም በሕጋዊ ማዕቀፍ እውቅና ኑሯቸው በተደራጀ አግባብ ስራቸውን እንዲያከናውኑ አሰራር ሳይዘረጋ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ የወጣውን መመሪያ መሰረት በማድረግ ለባሕላዊ የግጭት መፍቻ ፍርድ ቤቶች እውቅና የሚሰጥ አሰራር መዘርጋቱንና ለዚሁ የሚሆን የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ባሕላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች በቅርበት ለማሕበረሰቡ ተደራሽ በመሆን ዳኝነት በመስጠት፣ የመደበኛ ፍትሕ ስርዓቱን ስራ ከማቃለል ባለፈ የተገልጋዩን ጊዜና ወጪ በመቆጠብ ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በተደራጀና ሕጋዊ በሆነ አግባብ ስራቸውን እንዲያከናውኑ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ የመመሪያው ዝግጅት በመጠናቀቁ በቅርቡም ወደ ስራ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በክልሉ ሽምግልናን ጨምሮ አስራ አምስት ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓቶች እንዳሉ በጥናት መረጋገጡን ጠቅሰው፤ ለእነዚሕ ስርዓቶች ሕጋዊ እውቅና በመስጠት ሕብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ይደረጋል ብለዋል።


 

ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓቶች እውቅና እንዲያገኙና በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው ግጭቶችን እንዲፈቱ መደረጉ የክልሉ ባሕላዊ የችግር መፍቻ ስርዓቶች እንዲሰፉ እድል የፈጠረ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አየለ አናውጤ(ዶ/ር) ናቸው።

የባሕላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓቶች ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው እንዲሰሩ ማስቻል ባሕሉን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍም ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።

ክልል አቀፍ የሽምግልና መማክርት ጉባኤ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ጠቀሰው፤ ይህም ባሕላዊ የሽምግልና ስርዓቱን በማሳለጥ ድርሻው የጎላ እንደሚሆን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም