ቀጥታ፡

በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዘርፍ የስራ ዕድልን ለማስፋፋት የግሉ ዘርፍ ሚና የጎላ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዘርፍ የስራ ዕድልን ለማስፋፋት የግሉ ዘርፍ ሚና የጎላ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ”አረንጓዴ ስራዎች የተሻለ ነገ”  በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ፎረምና ባዛር  ማካሄድ ጀምሯል።


 

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ መንግሥት በመደመር እሳቤ በኢኮኖሚ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለትውልዱ ለማስረከብ በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

ባለሃብቶችና ኢንተርፕራይዞች በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዙሪያ ያላቸውን ፈጠራና የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያሳድጉ ፣ በተለይም በታዳሽ ሃይል ላይ የሚውል ካፒታል ፈሰስ ማድረግ፣ የኢኮኖሚ ኢኒሸቲቮችን ማገዝና ግብርናውን ማዘመን ላይ እንዲሳተፉ አሳስበዋል፡፡፡

ከነዚህ መካከል የሀገሪቱን የአየር ንብረት ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስራ ተጠቃሽ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ሽግግር በግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት፣ በአረንጓዴ ፈጠራ፣ ፋይናንስና ኢንተርፕርነርሺፕ ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በአረንጓዴ የኢኮኖሚ ዘርፍ የሚፈጠር የስራ ዕድል ለኢትዮጵያ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ተግባሩ  ከስራ፣ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ጋር ከተጣመረ ዘርፉን በፍጥነት ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመጠቀም የስራ እድል ፈጠራን ለማስፋፋት የያዘቸውን ግብ እንድታሳካ አጋር አካላት የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። 


 

በኢትዮጵያ የስዊድን ኤምባሲ ከፍተኛ የፕሮግራም ስራ አስኪያጅ የሆኑት ኒኮላ ኤሪክሰን አረንጓዴ የስራ ዕድል ፈጠራ ኢትዮጵያ በዘርፉ የጀመረችውን ሽግግር ለማገዝና የማይበገርና የተሰባጠረ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ 

ታዳሽ የሃይል አቅርቦትና ትራንስፖርት፣የአየር ብክለት ልቀት ቅነሳ፣የቆሻሻ አወጋገድ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዘርፍ በማደግ ላይ የሚገኙ አማራጮች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ይህንን እውን ማድረግ የሚችል በእውቀት የበለጸገና ጠንካራ ወጣት ሃይል አላት ብለዋል፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም