ቀጥታ፡

የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ የቱሪዝም ዘርፉን የሚያነቃቃ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ ታህሳስ 1/2018 (ኢዜአ)፡-የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ካለው ማህበራዊ ፋይዳ ባሻገር የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ እንደሚያነቃቃ ተገለጸ።    

የጊፋታ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም በሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት መመዝገቡን ተከትሎ የወላይታ ሶዶ ከተማና አካባቢው ህዝብ ዛሬ ደስታውን በሰላማዊ ሰልፍ ገልጿል።


 

የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" በወላይታ ብሔር አሮጌው ዓመት አልፎ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ሲሆን  በዓመቱም መስከረም ወር ላይ ይከበራል።

ወላይታዎች የዘመን መለወጫ በዓላቸውን ጊፋታን በዓሉን ሲያከብሩ ከአሮጌው ወደ አዲስ፤ ከጨለማ ወደ ብርሀን ስለሚያሸጋግርም እንደ ድልድይ ይቆጠራል።

ለሠላም፣  ለአብሮነትና ለእርስ በርስ ትስስር ጉልህ አስተዋጾ ያለው ጊፋታ በዩኔስኮ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት በመመዝገቡ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎች ዛሬ ደስታቸውን በአደባባይ ወጥተው ገልጸዋል። 

ደስታውን ለመግለጽ አደባባይ ለወጣው ህዝብ መልዕክት ያስተላለፉት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ (ረዳት ፕሮፌሰር) "ጊፋታ የወላይታ ብቻ ሳይሆን የዓለም ህዝቦች ቅርስ ሆኗል" ሲሉ ተናግረዋል።

በዓሉ ካለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አበርክቶ አንፃር ይበልጥ እንዲተዋወቅ የአሁኑ ትውልድ አደራ እንዳለበት ጠቅሰው፣ ጊፋታን ጠብቀው ላቆዩ አባቶችና በቅርስነት እንዲመዘገብ ለሰሩ  ሁሉ አመስግነዋል።

በዓሉ በዩኔስኮ መመዝገብ ካለው ማህበራዊ ፋይዳ ባሻገር የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ እንደሚያነቃቃ ገልጸዋል። 

የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማርያም በበኩላቸው የጊፋታ በዓል ከወላይታ ህዝብ ባለፈ የመላው ዓለም ቅርስ መሆኑ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ብዙ መለፋቱን ጠቅሰው "ተደምረን ከሠራን የማንሻገረው ተራራ እንደሌለ ይህ ማሳያ ነው" ብለዋል።

በዓሉን ጠብቆ በማቆየት ለትውልድ ለማሸጋገር እና በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በብዙ ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሱት ደግሞ የወላይታ ሀገር ሽማግሌ አቶ ባሳ ዳታ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ጊፋታ የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቦ በማየታቸው የላቀ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው፣ የአሁኑ ትውልድም የጊፋታን በዓልና እሴቶቹን ጠብቆ ማቆየትና ይበልጥ እንዲተዋወቅ ሀላፊነቱን እንዲወጣ አስገንዝበዋል። 


 

የወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል ዕሴቶች ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ ስመኝ ተደመ እና የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ አርቲስት ብዟየሁ ቡቼ በበኩላቸው "ጊፋታ" በዓለም ቅርስነት በመመዝገቡ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ጊፋታ ያሉት ትውፊቶችና እሴቶች ይበልጥ እንዲተዋወቁ በር እንደሚከፍት ተናግረው፣ በዓሉ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፉ ለማሳደግ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ ባስተላለፈው የእንኳን ደስ አላችሁ መልክት እንደገለጸው "ጊፋታ" በሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት መመዝገቡ በዓሉ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደትውልድ እንዲተላለፍና የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመር ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ጊፋታ በወላይታ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ በዓል ሲሆን የወላይታዎችም የማንነት መገለጫና የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ መሆኑ ይታወቃል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም