ቀጥታ፡

ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ ዐቅም ለመሸፈን የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 1/2018(ኢዜአ)፡- እየተከናወኑ ያሉ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ ዐቅም ለመሸፈን የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአማራ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

በክልሉ የነበረውን ሥር የሰደደ የተረጂነት አስተሳሰብና ተግባር ለመቅረፍ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ምክክሮች መደረጋቸውን የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሠርክአዲስ አታሌ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎም ከጠባቂነት መውጣትና እርስ በርስ የመደጋገፍ ዐቅምን ለማዳበር መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመው፤ ይህን በይበልጥ ለማስፋትና ለማጠናከር ቀጣይነት ያላቸው ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።

እንደመንግስት ከሚከናወኑ ተግባራት ባለፈ መረዳትን ባህል እንዳሆን የሚያስችሉ እና ህብረተሰቡ የምግብ ሉዓላዊነቱን እንዲያረጋግጥ የማድረግ ስራ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ ዐቅም ለመሸፈን ማምረት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነሯ አስገንዝበዋል።

እስካሁን በተሠሩ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመው፤ በዚህ ከቀጠልን ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ መሸፈን የሚያስችል ዐቅም እናዳብራለን ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም