በምዕራብ ጎንደር ዞን የበጋ ወቅት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን የበጋ ወቅት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ተጀመረ
ገንዳውሃ፤ ታህሳስ 1/2018(ኦዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን በተለያዩ ተፋሰሶች የበጋ ወቅት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
ዛሬ በተጀመረው በዚሁ ሥራ ላይ የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የፌዴራል ፖሊስና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን፤ ሥራው ለ30 ቀናት እንደሚቆይ ተነግሯል ፡፡
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አንዳርጌ ጌጡ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በዞኑ በአራት ወረዳዎችና ሶስት ከተማ አስተዳደሮች በሚተገበረው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ 2ሺ 300 ሄክታር የተጎዳ መሬት ይለማል።
ከዚህ ውስጥ በዛሬው ማስጀመሪያ ፕሮግራም በተለያዩ ቀበሌዎች 110 ተፋሰሶች ላይ መከናወኑን አንስተዋል።
የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ተግባር በወል መሬቶችና በግል ይዞታዎች የሚሰራ ሲሆን፤በዚህም የውሃ እቀባ፣ እርከን ሥራና ሌሎች ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።
በዘመቻ በሚካሄደው በዚህ የልማት ሥራ ከ36 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ለማሳተፍ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል።
አርሶ አደሮቹ የተፋሰስ ልማት ሥራዎቹን ቀጣይነት ያለው ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማጉላት በተለየው መሬት ላይ ዕፅዋቶች እንዲያለሙ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በሰሜን ምዕራብ ዕዝ የ504ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ቾምቤ ወርቁ በበኩላቸው፤ ሰራዊቱ ሰላምና ዳር ድንበርን ከማስከበር በተጨማሪ በልማት ሥራዎች በመሳተፍ ለሀገር እድገት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በበጋ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በተከናወነበት ሥፍራ ክረምት ላይ ችግኝ በመትከል የሚሳተፉ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዞኑ የገንዳውኃ ዙሪያ አርሶ አደር አየነው ያሲን በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት ዓመታት በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ላይ ተሳትፈው መልካም ውጤት በማየታቸው በዚህ ዓመት ሥራውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በወል መሬት ላይ በተከናወነው እርከንና ችግኝ ተከላ ልማት አፈሩ ተሸርሽሮ ከጥቅም ውጭ የነበረ ስፍራ አገግሞ ለከብት መኖና የከርሰ ምድር ውሃን በማጎልበት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸውም አውስተዋል።
በበጋ የአፈርና ውሃ የጥበቃ ሥራዎች የለሙ ተፋሰሶች ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የገለጹት ሌላኛው አርሶ አደር የሱፍ ዳምጤ ናቸው።