ትውልድን በሥነ ምግባር መገንባትና ተቋምን በግልጽ አሠራር መምራት ሙስናን የመከላከል ቁልፍ ተግባሮቻችን ናቸው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ትውልድን በሥነ ምግባር መገንባትና ተቋምን በግልጽ አሠራር መምራት ሙስናን የመከላከል ቁልፍ ተግባሮቻችን ናቸው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፦ ትውልድን በሥነ ምግባር መገንባትና ተቋምን በግልጽ አሠራር መምራት ሙስናን የመከላከል ቁልፍ ተግባሮቻችን ናቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ በ22ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን የበዓል ማጠቃለያ መድረክ ላይ ተገኝተናል ብለዋል።
ሙስናን እንደ ብሔራዊ አጀንዳ እና ለብልጽግናችን ቀይ መሥመር አድርገን በመውሰድ በጸና አቋም ትግላችንን አጠናክረን ቀጥለናል ሲሉም ገልጸዋል።
መንግሥት የፀረ ሙስና ትግሉን ውጤታማ ለማድረግ በወሰዳቸው የሪፎርም ርምጃዎች ሀገርን ሊያፈርስ የደረሰውን ተቋማዊ ሙስና አስቀርቷል ብለዋል።
በሙስና የተመዘበረ ሀብትን የሚያስመልስ ዐዋጅን አጽድቋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍትሕ ተቋማቱ ላይም ሰፊ ሪፎርምን እያካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል።
የመንግሥት አገልግሎትን ግልጽና ቀልጣፋ ለማድረግ የከፈትናቸው የመሶብ ማዕከላት አስተዳደራዊ ሙስናን እየተከላከሉ የዜጎችን የአገልግሎት ርካታም እያሳደጉ ይገኛሉ ብለዋል።
ዜጎች ያለ ሥጋት የሙስናን ወንጀል ጥቆማ የሚሰጡበት ዲጂታል ሥርዓትም ተግባራዊ ተደርጓል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ሙስናን ለመከላከል ዘላቂ መፍትሔው ትውልድን በሥነ ምግባር መገንባት፣ ተቋማትን ከብልሹ አሠራር መከላከል እና ለሙስና ወንጀል ተገቢውን የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በመሆኑም የፀረ ሙስና ትግሉ ስኬታማ እንዲሆን እና የመሶብ አገልግሎት እንዲጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።