ቀጥታ፡

በፀረ ሙስና ትግሉ የተቋማትን ግልፅነትና ተጠያቂነት ማጠናከር ወቅቱ የሚፈልገው የቤት ሥራ ነው 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡- በፀረ ሙስና ትግሉ የተቋማትን ግልፅነትና ተጠያቂነት ማጠናከር  ወቅቱ የሚፈልገው የቤት ሥራ መሆኑን የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) ገለጹ።

የ22ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን ማጠቃለያ  " ትውልድን በሥነ ምግባር፣ ተቋማትን በአሠራር" በሚል መሪ ሀሳብ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህና ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከብሯል።  


 

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ(ዶ/ር)፥ በኢትዮጵያ በህዳር በተካሄደው የፀረ ሙስና ቀን አከባበር የተቋማትን የፀረ ሙስና ባህል የማጎልበት፣ የአሠራር ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የግንዛቤ መፍጠርና የማነቃነቅ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።  

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ኮንቬንሽንን በመፈረም ተቋም አቋቁማ ህጎችን በማውጣት እየተገበረች ትገኛለች ብለዋል።  

ሆኖም ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ህዝቡ ሙስናን በባለቤትነት እንዲታገል አለማድረግ፣ የሥነ ምግባር ግንባታ ትኩረት መነፈግ፣ በተቋማት ግልፅነትና ተጠያቂነትን ያለማስፈን ጉድለቶች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።  

በዚህም የሥርዓታዊና ተቋማዊ የሙስና ምልክቶች መታየታቸውን እና ደካማ የሙስና መከላከል አፈጻጸም መመዝገቡን አስታውሰዋል።  

የለውጡ መንግሥት ይህን መሠረታዊ ችግር በመገምገም ህጎችን በማሻሻል፣ ተቋማዊ አሠራርን በማዘመን፣ ትብብሮችን በማጠናከርና የተሟላ የተቀናጀ የሙስና መከላከል ስትራቴጂ መተግበር መጀመሩን ገልጸዋል።  

የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ  እንዲሁም የተቋማት ግልፅነትና ተጠያቂነት አሠራር እየተጠናከረ መምጣቱን አንስተዋል።  

የፍትሕ አካላትን አቅም የሚያጠናክሩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በተወሰዱ የፀረ ሙስና ተግባራት በሙስና ለችግር ተዳርገው የቆዩ የልማት ድርጅቶች ቁመና ተስተካክሏል ብለዋል።   


 

ሥርዓታዊና ተቋማዊ ሙስና እንዳይኖር በማድረግ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ማምጣታቸውን ጠቅሰው፤ አሁንም አስተዳደራዊና ቢሮክራሲያዊ ጉዳዮችን  በመጠቀም ሙስና የሚፈፅሙ መኖራቸውን አንስተዋል።  

ለአብነትም ህግ ያልተከተሉ የግዥ አሠራሮች፣ የፕሮጀክት ውሎች መዛነፍ፣ የሰነዶችና የመሬት አስተዳደር ላይ የሚታዩ ችግሮች፣ የህዝብ አገልግሎትን በእጅ መንሻ የማቅረብ ፈተናዎችን ጠቅሰዋል።  

በመሆኑም የለውጡ መንግሥት የዘረጋውን የፀረ ሙስና ትግልና የሪፎርም አቅጣጫ በተሟላ መንገድ በመፈጸም ለሙስና በር የሚከፍቱ አካሄዶችን ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል።  

ተቋማዊ የአሠራር ግልፅነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንዲሁም በየቦታው ተሰግስገው አስተዳደራዊ ሙስና የሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰድ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም