ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት ተቋማዊ ሙስናን አምርሮ በመጠየፉና በማስቆሙ ታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡- የመደመር መንግሥት ተቋማዊ ሙስናን አምርሮ በመጠየፉና በማስቆሙ ታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

22ኛው የዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን  "ትውልድን በሥነ ምግባር፣ ተቋምን በአሰራር" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከብሯል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሙስና የሞራል ውድቀት እና የተቋማት ድክመት ድምር ውጤት እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ይህን አስከፊ ተግባር ለመከላከል ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ጀምሮ የሕግ ማዕቀፍና ተቋም አቋቁማ እየሠራች ትገኛለች ብለዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ በማቋቋም ጭምር፤ ሀገራዊ የሙስና ወንጀል አዝማሚያን ለመገምገም፣ ግንዛቤ ለመፍጠር እና ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማመልከት የሚያስችሉ የንቅናቄ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

ሀገራዊ ስኬቶች እየተመዘገቡ ያሉት የመደመር መንግሥት መንግስታዊ ሙስናን አምርሮ የሚጠየፍ በመሆኑ ነው ብለዋል። 

ለአብነትም በሪፎርም የተቃኙ ተቋማት ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን እየተዋጉና ብልሹ አሰራርን በፍጥነት እያረሙ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፣ ኪሳራ ውስጥ የቆዩ የልማት ድርጅቶች ትርፋማ ሆነው የበጀት ጉድለት መሙላት እና ተሸላሚ ግብር ከፋይ መሆናቸው፣ መንግስታዊ ሌብነትን የመፀየፍ ማሳያዎቻችን ናቸው ብለዋል።

በሙስና እና በሌሎች ወንጀሎች የሚመዘበር የሕዝብ ሀብት በውጤታማነት እንዲመለስ አስቻይ ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ ከዚህ በፊት ጉድለት ያለበትን የንብረት ማስመለስ ዐዋጅ መሻሻሉን ጠቅሰዋል።

በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ እንደ መሶብ አንድ ማዕከል ዓይነት አዳዲስ የአሠራር መንገዶች የተዘረጉት ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን በመፍጠር ሙስናን ለመከላከል መሆኑንም ጠቅሰዋል።


 

በሌላ በኩል ሙስናን የመከላከል ዘላቂ መፍትሔው የትውልድን ሥነ ምግባር በመገንባት እና ለሙስና የማይበገር ዜጋ በመፍጠር መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

ተቋማዊ በመሆን ሀገር ወደ ማፍረስ ደረጃ እያመራ የነበረውን ሙስና በጠንካራ ትግል አስቁመናል ነው ያሉት። 

የትውልድን ሥነ ምግባር መገንባት፣ ተቋማዊ አሠራርን በማዘመን ከሙስና መከላከል፣ ለሙስና ወንጀል ሕግ መከበር ሁሉም ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም