ቀጥታ፡

የአካባቢያችንን ጸጋ በመለየት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንሰራለን-አመራሮች

ሚዛን አማን፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡- እይታችንን አስፍተን የአካባቢያችንን ጸጋ በመለየት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉ የቤንች ሸኮ ዞን አመራሮች ገለጹ።

ላለፉት ቀናት "የመደመር መንግስት እይታ በዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ የተሰጠውን ስልጠና የተከታተሉ የቤንች ሸኮ ዞን አመራር አባላት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ እይታችንን አስፍተን የአካባቢያችንን ጸጋ በመጠቀም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል።

የደቡብ ቤንች ወረዳ አመራር የሆኑት አቶ ኃይሌ ግዛት እንዳሉት፤ የመደመር መንግስት ሀሳብን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማሳካት የሚያስችል በቂ ሥልጠና መሰጠቱ አጋዥ አቅም እንደሆናቸው ጠቁመዋል።


 

አካባቢያችን የቱሪዝም፣ የማዕድን እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ያልተነኩ ሀብቶች ያለበት በመሆኑ ሠርቶ ውጤት ማምጣት ከአመራሩ ይጠበቃል ብለዋል።

የዜሮ እና የመጨመር ተግባራትን በአግባቡ ለይቶ በመምራት ከግብ እንዲደርሱ ህዝቡን በማስተባበር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በምግብ ራስን የመቻል ውጥንን እውን ለማድረግ ከሰብል ልማት ባሻገር የፍራፍሬ፣ የጓሮ አትክልት፣ የቅመማ ቅመም፣ የማርና ቡናን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የአካባቢው እምቅ አቅሞችን በእጥፍ ምርት ለማረጋገጥ መሥራት አለብን ነው ያሉት።

ከመደመር መንግስት ግቦች መካከል ተረጂነትን ዜሮ ማድረግ፣ መሬት ጾም እንዳያድር ማድረግና ለሌማት ትሩፋት ሥራ ያለውን ተስማሚነት ተጠቅሞ ምርቶችን ማሳደግ እንደሚጠበቅ የሼይ ቤንች ወረዳ አመራር አቶ ወንድሙ ጌታ ተናግረዋል።


 

እነዚህን የመንግስት የልማት ግቦች ወደ ውጤት ቀይሮ የሕዝብ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ራዕይ ይዘው ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እይታችንን ባለ ማስፋታችን ለውጥ ያላመጣንባቸውን የልማት ዘርፎች በመደመር መንግሥት እይታ ለይተን ተጠቃሚ ለመሆን ተዘጋጅተናል ያሉት ደግሞ ሌላዋ አመራር ወይዘሮ ባንቻየሁ ሉቃስ ናቸው።

የተለያዩ የልማት ተሞክሮዎችን በመቀመር በቀበሌ ደረጃ ለማስፋት እንደሚተጉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም