ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል 18 ሚሊዮን ኩንታል ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ይቀርባል

መቱ ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል  የቡና ምርትና ጥራትን በማስጠበቅ በምርት ዘመኑ 18 ሚሊዮን ኩንታል ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ  እየተሰራ መሆኑን  የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እና የዞኑ አመራሮች በኢሉባቦር ዞን የተለያዩ ወረዳዎች እየተሰበሰበ የሚገኘውን የቡና ምርት ጥራትና አያያዝ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የቡናን ምርታማነትና ጥራትን በማሻሻል በገበያ ተወዳዳሪነቱን የተሻለ  ለማድረግ ኢንሼቲቭ ተቀርጾለት እየተሰራ መሆኑ ነው የተመላከተው።


 

የቡና ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግም ያረጁ የቡና ዛፎችን ከመጎንደልና በአዲስ ከመተካት ባለፈ፣ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የቡና ችግኞችን ማዘጋጀት  ላይም ትኩረት ተሰጥቷል።

ለዚህም በቡና ልማትና ጥራት ፓኬጅ ላይ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች  የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ  መደረጉም ታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ  እንዳሉት፤ በክልሉ የቡና ልማትና ጥራትን በማስጠበቅ በምርት ዘመኑ 18 ሚሊዮን ኩንታል  ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ  እየተሰራ ነው።

የቡና ጥራትን ለማረጋገጥ  ቀይ እሸት ቡና በመልቀምና  በአልጋ ላይ በማድረቅ በክምችትና በማጓጓዝ ብክለት እንዳይከሰት ክትትል እየተደረገ መሆኑን አንስተው፤ በእስካሁኑ እንቅስቃሴ 8 ሚሊዮን ኩንታል መሰብሰቡን ተናግረዋል።


 

ከቡና የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግም ከቡና ልማት እስከ ምርት አሰባሰብ  ድረስ ለምርት ጥራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በኢሉባቦር ዞን በቡና ከለማው  342 ሺህ ሔክታር መሬት በቡና መልማቱንና ከዚህም 74 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ‎አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ናቸው።

በዞኑ በቡና ንግድ ስራ ላይ 22 ማሕበራት መሰማራታቸውንና ለጥራቱም ትኩረት እንዲሰጡ ግንዛቤ እንደተሰጣቸውም አስረድተዋል።


 

የቡና ምርት ጥራትን  በማስጠበቅ  የአምራቾች እና አቅራቢዎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን  ለማሳደግ ህገወጥ ንግድን መቆጣጠር ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አቶ እንዳልካቸው አንስተዋል።

በዞኑ የመቱ ወረዳ ነዋሪ  አርሶ አደር  ደሳለኝ ተፈሪና አቶ ገመቹ ተካ  በበኩላቸው ቀይ  ቡናን  በመልቀምና በአልጋ ላይ  በማድረቅ ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም