የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የራስ ገዝነት ጥያቄ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎችን አቅም ለማጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የራስ ገዝነት ጥያቄ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎችን አቅም ለማጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡- የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የራስ ገዝ አስተዳደር የምርምር ዩኒቨርሲቲዎችን አቅም በማጎልበት የትምህርት ጥራትና ውጤታማነትን ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና እንዳለው የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
የባህርዳር፣ ጅማ፣ ጎንደር፣ እንዲሁም የአዳማና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝነት ጥያቄ ማቅረባቸውም ተገልጿል።
በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና መሰረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥራት ውጤታማነትን እንዲያስጠብቁ ትኩረት ተሰጥቷል።
የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የራስ ገዝነት ሽግግር በአስተዳደር፣ በሰው ሃብት፣ በፋይናንስና አካዳሚክ ምርምር ውጤታማነት ቁመናን መሰረት ተደርጎ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተደራሽነትን ለማስፋት ውጤታማ ስራ ቢከናወንም የትምህርት ጥራትና ተወዳዳሪነትን ከማስጠበቅ አኳያ ግን ውስንነቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
በሀገራዊ ለውጡ ማግስትም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከተከናወኑ ተግባራት በተጓዳኝ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የራስ ገዝ አስተዳደር የሚያገኙበት ሥርዓት መፈጠሩን አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችለውን የሁለት ዓመት የሽግግር ጊዜ አጠናቆ ወደ ሙሉ ራስ ገዝነት በመሸጋገር ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይም ተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ ራስ ገዝነት ለማሸጋገር የሚያስችሉ መመሪያዎችና አሰራሮች በትምህርት ሚኒስቴሩ መዘጋጀቱንና በዚሁ መሰረት ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ አመላክተዋል ፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች በአስተዳደር፣ በፋይናንስ፣ በሰው ሃብት፣ በአካዳሚክ ጉዳዮችና በምርምር ዘርፍ ያላቸውን ቁመናና የሚያስመዘግቡትን ውጤት መሰረት በማድረግ ወደ ራስ ገዝነት ይሸጋገራሉ ብለዋል፡፡
ይህም የምርምር ዩኒቨርሲቲዎችን አቅም በማጎልበት የትምህርት ጥራትና ውጤታማነትን ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በመሆኑም አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ባህርዳር፣ ጅማ፣ ጎንደር፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝነት ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል፡፡
በመላው ሀገሪቱ ከሚገኙ 52 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች 47 ዩኒቨርሲቲዎች ለትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡