ቀጥታ፡

በክልሉ በተከታታይ እየተተገበረ የሚገኘው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው

አምቦ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል በተከታታይ እየተተገበረ የሚገኘው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ መምጣቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በዞኑ በወልመራ ወረዳ በበጋ መስኖ የሚለማ ስንዴ የዘር መዝራት መርሃ ግብር የክልሉ፣ የዞንና የወረዳው የስራ ኃላፊዎች  በተገኙበት ተካሄዷል።


 

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደጀኔ ሂርጳ እንዳሉት፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከታታይ እየተተገበረ የሚገኘው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ  ነው።

ዘንድሮም በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች አርሶ አደሩ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መሳተፍ እንዲችል የግብዓት፣ የቴክኖሎጂ እና የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።


 

በምዕራብ ሸዋ ዞንም አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም ተደራጅቶ የበጋ መስኖ ስንዴን ማልማት መጀመሩን ገልጸው በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተረፈ አራርሳ በበኩላቸው፤ በዞኑ በበጋው መስኖ 400 ሺህ ሔክታር መሬት ይለማል ብለዋል።


 

በእስካሁኑ ሂደትም 200 ሺህ ሄክታር መሬት የማሳ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው ልማቱን ስኬታማ ለማድረግ የግብዓት አቅርቦት በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

የወልመራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና እና መሬት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ሂርጳ፤ የወረዳው አርሶ አደሮች የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን እየተለማመዱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።


 

በዚህም በወረዳው ምርትና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ገልጸው በዘንድሮ በጋ ወራት 25 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 21 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡

የወረዳው አርሶ አደሮች ባለፉት ዓመታት ስንዴን በበጋ መስኖ በማልማት ተጠቃሚነታቸው እያደገ፤ ኑሯቸውም እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል። 

አርሶ አደር ድሪባ በቀለ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በጋራ በመሆን በኩታ ገጠም የበጋ ስንዴ እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የበጋ ስንዴን በኩታ ገጠም ማልማት ሳይጀመሩ በፊት በሄክታር ትንሽ ምርት ሲያገኙ መቆየታቸውን አንስተው ዘንድሮ ከሄክታር 30 ኩንታል ስንዴ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኩታ ገጠም ልማቱም የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ እገዛ እያደረጉላቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ሌላው አርሶ አደር ባዩ ጐንፋ፤ በተያዘው በጋ በመስኖ የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን  በመግለፅ በሙሉ አቅም ወደ ስራ መግባታቸውን አስረድተዋል።


 

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱም ኑሯቸው እየተሻሻለ፤ ተጠቃሚነታቸውም እያደገ በመምጣቱ በተያዘው በጋም የተሻለ ምርት ለማግኘት ዘር መዝራት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም