ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሊየር ልማት መርሃ ግብር ፈጣን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገቷን ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል  

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሊየር ልማት መርሃ ግብር በአስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ፈጣን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገቷን ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመረቀበት ወቅት የ30 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማብሰራቸው ይታወሳል።

የጉባ ብስራት ከሆኑት ብሔራዊ ፕሮጀክቶች ውስጥም ግዙፍ የአየር ማረፊያ፣ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቤቶች፣ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታና ሰላማዊ የኒውክሊየር ልማት መርሃ ግብር ይገኙበታል።

በኅዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እና የባለድርሻ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የኢትዮጵያን የኒውክሊየር ኃይል ልማት መርሃ ግብር ማስጀመሪያና የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ ተካሂዷል። 

በማስጀመሪያ መድረኩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኢነርጂ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ፣ የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሚካኤል ቹዳኮቭና የባለድርሻ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት በዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ የቴክኒክ ትብብር መምሪያ የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍል ዳይሬክተር ጋሻው ገበየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላትና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች የምትገኝ ሀገር ናት።

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ለማፋጠንም አነስተኛ የካርቦን ልቀት ያለው አስተማማኝ የኒውክሊየር ኃይል አቅርቦት ወሳኝና ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲም በቴክኒክ ትብብር አማካኝነት ለኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሊየር ልማት መርሃ ግብር አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የኒውክሊየር ሳይንስና ቴክኖሎጂ በግብርና፣ ጤና፣ ኢንዱስትሪ፣ ውሃና በአካባቢ ጥበቃ አስተዳደር ሥርዓት የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳለጥ ወሳኝ መሳሪያ መሆኑን አንስተዋል።

የኒውክሊየር ልማት መርሃ ግብር በአስተማማኝ የኤሌክትሪክ የኃይል አቅርቦት በአነስተኛ የካርቦን ልቀት ለአካባቢ ሥነ-ምኅዳር ደኅንነት ተመራጭ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያም አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን በመፍጠር የግብርና፣ ኢንዱስትሪና ሌሎች የኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ የኒውክሊየር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማትን የሚያሳልጥ ብቁ ሰው ሃይል ማፍራት እንደሚኖርባት አስገንዝበዋል።

የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም