ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ እያከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትና የኃይል ስርቆት የሚፈጽሙ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ የወንጀል ክስ መመስረቱን ገለጸ።

አገልግሎቱ ባለፉት አራት ወራት በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማትና በሀይል ስርቆት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎችን በመለየት አስሩ ላይ የወንጀል ክስ መመስረቱን አመልክቷል።

አገልግሎቱ ባለፉት አራት ወራት በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማትና በሀይል ስርቆት ዙሪያ የተፈፀሙ ወንጀሎችና የተሰጡ መፍትሔዎችን በሚመለከት የተቋሙ የስራ ሀላፊዎች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአገልግሎቱ የኮሙዩኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር እንደገለፁት፤ ባለፉት አራት ወራት የትራንስፎርመር፣ የኬብል፣ የመኪና አደጋ እና የሀይል ስርቆት ወንጀሎች አጋጥመዋል።

ባለፉት አራት ወራት ብቻ ባደረገው የቁጥጥር ስራ 107 ወንጀሎችን በመለየት ተጠያቂነትን ለማስፈን ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት።

ከእነዚህ ውስጥ አስር የወንጀል ክሶች መመስረታቸውን ገልፀው፤ ጉዳዩ በፍርድ ሒደት ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

ይሁን እንጂ ተቋሙ በሚያደርገው የቁጥጥር ስራ ብቻ ችግሩን ማስቆም እንደማይቻል ጠቁመው፤ ማህበረሰቡ በባለቤትነትና በሀላፊነት ከተቋሙ ጋር በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የህግና ስነ-ምግባር ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ አበበ ተስፉ በበኩላቸው፤ በየትኛውመ መልኩ የሚደርስ የመሰረተ ልማት ስርቆትና ጉዳት የሃይል አቅርቦት ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድር መገንዘብ ያስፈልጋልም ብለዋል።

በመሆኑም የመሰረተ ልማት ጥበቃና የሃይል አቅርቦትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል የህግ ስርዓት ተዘርግቶ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ውድመት በዜጎችና በሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ታሳቢ በማድረግ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የማርኬቲንግ፤ሽያጭና ደንበኞች አገልግሎት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ብርሃኑ አልጅራ ተቋሙ ቀደም ሲል በስርቆትና መሰል ወንጀሎች ላይ የሚጥለው ቅጣት እምብዛም እንደነበር አስታውሰዋል።


 

በመሆኑም የቁጥጥር ስረዓቱን ከማጠናከር ባሻገር የቅጣት አወሳሰኑን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን በማመን ተመጣጣኝና አስተማሪ የቅጣት አወሳሰን ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ መሰረት ከኃይል አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በየደረጃቸው የሚጣልባቸው የገንዘብ ቅጣት ወጥነት ባለው መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ ስለመሆኑ ነው የጠቆሙት።

ይህ የቅጣት አወሳሰን ወንጀለኞች የሚጠበቅባቸውን ማሻሻያ ካላደረጉ ቅጣቱ በእጥፍ  እንደሚሆንም አረጋግጠዋል።

 

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም