ማዕከሉ በምርምር የወጡ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን እያባዛ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ በምርምር የወጡ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን እያባዛ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ ነው
አዳማ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡- የቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር የወጡ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎች እያባዛ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ አስታወቀ።
በምርምር የወጡ የስንዴ ዝርያዎች በሄክታር እስከ 72 ኩንታል ምርት የሚሰጡ እንደሆኑ ተመልክቷል።
የምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ አለማየሁ ለኢዜአ እንዳመለከቱት ፤ ማዕከሉ በሀገሪቱ የስንዴ ምርምር ብሔራዊ ማስተባበሪያ ሆኖ እየሰራ ይገኛል።
"መልካ፣ ጉቱ፣ አስጎሪ፣ ዳካ" እና ሌላም ስያሜ የተሰጣቸው የተለያዩ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን በማባዛት ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በምርምር የወጡ የስንዴ ዝርያዎች ቢጫ ዋግና የስንዴ ራስ አድርቅ በሽታዎችን በመቋቋም ከተለመደው የስንዴ ዝርያ የበለጠ ከፍተኛ ምርት መስጠት እንደሚችሉ በምርምር ሂደት ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል።
የተሻሻሉት የስንዴ ዝርያዎች በማዕከሉ በሄክታር እስከ 72 ኩንታል፤ በአርሶ አደር ማሳ ደግሞ እስከ 61 ኩንታል በሄክታር መስጠት እንደሚችሉ አስረድተዋል።
በማዕከሉ እስከ አሁንም 113 የስንዴ ዝርያዎች በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ መደረጉን ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ ከወረር እና ከቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር 45 የማካሮኒ እና ፓስታ "ዱረም" የተሰኙ የስንዴ ዝርያዎች በምርምር ማውጣት መቻሉንም አንስተዋል።
የቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የሚያወጣቸውን የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎቸን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረጉን ተግባር አጠናክሮ መቀጠሉንም አስታውቀዋል።
ሀገሪቱ በምግብ ራስን በመቻል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት ማዕከሉ ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በዚህም የምርምር ማዕከሉ በግብርና ዘርፍ እየተተገበሩ ያሉትን ኢኒሼቲቮችና የሽግግር ሂደቱን በግንባር ቀደምትነት በቴክኖሎጂና አዳዲስ አሰራር እያገዘ ይገኛል ነው ያሉት።
በተጨማሪ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የስንዴ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት አባዝቶ መነሻ ዘር እያቀረበ እንደሚገኝም አብራርተዋል።