በክልሉ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳልጡ የሪፎርም ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳልጡ የሪፎርም ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ባህር ዳር ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና ዘመኑን የሚመጥን ለማድረግ የሚያስችሉ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ገለጸ።
በቢሮው የሪፎርም ድጋፍና ክትትል ዳይሬክተር አቶ እንዳላማው ይታይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከሃምሌ 2017 ዓ.ም ጀምሮ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ የታገዘና ወቅቱን የሚመጥን እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ነው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የፀደቀውን የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ መሰረት በማድረግ ከፌደራል መንግስቱ ተናባቢ በሆነ አግባብ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ግልጽና ቀልጣፋ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ የህዝብን አገልግሎት የማግኘት ፍላጎት በሚያረካና ቅሬታዎችን ሊመልስ በሚችል መልኩ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ፣ ዲጂታላይዝድና ዘመኑን የሚመጥን መሆን እንደሚጠበቅበት ገልጸው፤ ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ሪፎርሙ ብዝሃነትና አካታችነት ያለው፣ ነጻና ገለልተኛ እንዲሆን ጭምር ተደርጎ እየተሰራ ያለው።
ሪፎርሙ ለተመደበበት ሙያ ብቁና ዲጂታላይዝድ የሆነ ሲቪል ሰርቫንት መፍጠርን መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ቅቡልነት ያለው የመንግስት ሰራተኛ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።
ብቃት ያለው አመራር፣ ባለሙያና ተቋም በመፍጠር ተዓማኒነት ያለው አገልግሎትን መዘርጋት ግድ የሚልበት ጊዜ መሆኑን ገልጸው "መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሪፎርም ስራዎች መካከል አንዱ "መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በክልል ደረጃ እንዲሁም በባህር ዳርና ደሴ ከተማ አስተዳደሮች ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ግልጽና በርካታ ጉዳዮችን በአንድ ጊዜ እልባት የሚሰጥና ህብረተሰቡ ባለበት ቦታ ሆኖ ያለምንም እንግልት አገልግሎቱን እንዲያገኝ ያስቻለ የሪፎርሙ አካል ነው ብለዋል።
በሌሎች አካባቢዎችም እስከ ወረዳ ድረስ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት፣ የባለሙያውን የአቅም ክፍተት በተለያዩ ስልጠናዎች ማብቃትና ተዓማኒና ግልጽ የሆነ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት የሪፎርሙ አካል መሆናቸውን ገልጸዋል።
የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርሙ ሦስት ዓመት የሚወስድ መሆኑን ጠቅሰው፤ በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።