ቀጥታ፡

የጅማ ከተማ የኮሪደር  ልማት የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር አስችሏል

ጅማ ፤ ታህሳስ 1/2018(ኢዜአ)፡- የጅማ ከተማ የኮሪደር  ልማት ከተማዋን ውብ እና ማራኪ በማድረጉ የጎብኚዎች ቁጥር መጨመሩን የከተማው ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የኮሪደር ልማት በስፋት ከተካሄደባቸው ከተሞች መካካል ጅማ ተጠቃሽ ስትሆን በከተማው የተሰራው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከማስዋብ ባለፈ በርካታ እድሎች ይዞ የመጣ መሆኑ ተመልክቷል።


 

ከእድሎቹ መካከል በከተማው የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረግ አንዱ ሲሆን በተለያዩ ዘርፎች የተፈጠረው የስራ እድልም ይጠቀሳል።

የጅማ ከተማ የቱሪዝም ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሮዚ ዛኪር እንደተናገሩት፤ በጅማ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ለነዋሪ ብቻ ሳይሆን ለጎብኚዎችም ምቹ አድርጓታል።


 

በኮሪደር ልማት ስራው የአገር ውስጥ እና የውጪ አገር ጎብኚዎች ቁጥር መጨመሩን ጠቅሰው ባለፈው ዓመት ከ1 ሺህ በላይ የውጪ አገር ጎብኚዎች ከተማዋን ጎብኝተዋል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በርካታ የአገር ውስጥ እና የውጪ ጎብኝዎች ጅማን እየጎበኙ መሆኑን ጠቁመው ጎብኚዎቹ በዋናነት የአባጅፋር ቤተመንግስት እና የቦዬ ሀይቅን እየጎበኙ ነው ብለዋል።


 

በከተማዋ የኮሪደር ልማት ስራ የጎብኚዎች ቁጥር ከመጨመር ባለፈ ጅማን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን እድል እየፈጠረላት መሆኑንም አስረድተዋል።


 

በከተማዋ በተገነባው የኮሪደር  ልማት የጎዳና ላይ ፎቶ የስራ እድል የተፈጠረላቸው የከተማው ወጣቶችም ኮሪደር ልማቱ ገቢ እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል።

ወጣቶቹ  በከተማዋ አደባባዮችና ጎዳናዎች በኮሪደር ልማቱ ላይ የእግር ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎችን ፎቶ በማንሳት ገቢ እያገኙ ይገኛሉ።


 

በከተማዋ ኮሪደር ልማት አማካኝነት በተፈጠረላቸው የስራ እድል ደስተኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በጅማ ከተማ የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ በዋና ዋና መንገድ ዳር የቡና መሸጫ ቤቶች፣ ፈጣን ምግቦች መሸጫ እና የእንጨት ውጤቶች መሸጫ  ሱቆች በብዛት ስራ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም